ጋና በአንድ ቀን አምስት ሚሊዮን ችግኝ የመትከል እቅድ እንዳላት አስታወቀች

ታትሟል

የምዕራብ አፍሪካዊት አገር ጋና በአንድ ቀን ውስጥ አምስት ሚሊዮን ችግኞች የመትከል እቅድ እንዳላት አስታውቃለች።

የአገሪቱን ደን ለማላበስ በተያዘው ዕቅድ በዛሬው ዕለት ጋናውያን በሙሉ ችግኝ እንዲተክሉ ጥያቄ ቀርቦላቸዋል።

የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ናና አኩፎ አዶ በበኩላቸው ከዚህ በኋላ አመታዊ ዝግጅት እንዲሆን በታቀደው ችግኝ ተከላም እንደሚገኙ አስታውቀዋል።

ፕሬዚዳንቱ ለህዝቡ ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክትም ዜጎች ከባቢያቸውን ለመጠበቅ ችግኞችን በመትከል የራሳቸውን አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ ነው።

ችግኞቹ በአብዛኛው በተሸረሸሩ መሬቶች የሚተከሉ ሲሆን በተጨማሪም በቤተ ክርስቲያን ግቢዎች እንዲሁም በሰዎች ቤቶች ይተከላሉ ተብሏል።

የጋና ባለስልጣናት እንደሚገምቱት የአገሪቱ የደን ሽፋን ከአውሮፓውያኑ አቆጣጠር 1900 ጀምሮ እንደተመናመነ ነው።

ከዚህም ጋር ተያይዞ ጋና የአየር ንብረት ለውጥ ተፅእኖ ተጋላጭ ሆናለችም ተብሏል።

ይህም ሁኔታ የምርት መቀነስ ያስከተለ ሲሆን በመጪው አስርት አመታትም በአገሪቱ ውስጥ ያሉ የእህል ምርቶች 7 በመቶ እንደሚቀንሱ ተጠቁሟል።