በታንዛንያ 'ጠበቅ ባለ ሱሪ' ምክንያት ከፓርላማ የተባረሩት የምክር ቤት አባል ጉዳይ ቁጣን ቀሰቀሰ

የፎቶው ባለመብት, @Hakingowi
በታንዛንያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት ሴት ፖለቲከኛ በሱሪያቸው ምክንያት ከፓርላማው መባረራቸው ቁጣን ቀስቅሷል።
የታንዛንያ ሴት ምክር ቤት አባላት ይፋዊ የሆነ ይቅርታም ያስፈልጋል እያሉ ነው።
አንድ የፓርላማው አባል በያዝነው ሳምንት ማክሰኞ ሴቶች በአለባበሳቸው ምክንያት ፓርላማውን እየዘለፉት ነው ሲሉ ወቅሰው ነበር።
በዚህም አላበቁም "አፈ ጉባኤ ለምሳሌ ያህል ቢጫ ሸሚዝ ያደረገችውን እህቴን ሱሪዋን ይመልከቱት" በማለት ሁሴን አማር የተባሉት የምክር ቤት አባል በቁጣ ተናገሩ።
ይህንንም ተከትሎ የፓርላማው አፈ ጉባኤ ኮንደስተር ሲችዋሌ የተባሉትን የፓርላማ አባል እንዲወጡ ነገሯቸው።
"ቤትሽ ሂጂና በስርዓት ለብሰሽ መጥተሽ ትሰበሰቢያለሽ" በማለት አፈጉባኤ ጆብ ንዱጋይ ተናገሩ።
አፈጉባኤው አክለውም በሴቶች የፓርላማ አባላት አለባበስ ላይ ወቀሳ ሲቀበሉ ይህ የመጀመሪያቸው እንዳልሆነና "ያልተገባ ልብስ የለበሱ" የፓርላማ አባላት መግባት እንዲከለከሉም ለምክር ቤቱ ህግ አስከባሪ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።
ሴት የፓርላማ አባሏን "አለባበሷ ያልተገባ ነው" ያሉት ሁሴን ምን እንደሆነ ዝርዝር ባይናገሩም የምክር ቤቱን የአለባበስ መመሪያ ጠቅሰዋል።
በመመሪያው መሰረት ሴቶች ሱሪ እንዲለብሱ ቢፈቅድም ጠበቅ ያለ መሆን የለበትም በማለት ሁሴን ተከራክረዋል።
ቢቢሲ አስተያየታቸውንም ፈልጎ ቢጠይቅም ግለሰቡ ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም።
ጃኩሊን ንጎንያኒና ስቴላ ማንያንያ በሚባሉ የሴት የምክር ቤት አባላት የሚመራ ቡድንም የተቋቋመ ሲሆን የፓርላማው ውሳኔ ትክክልም አይደለም ሲሉ ተቃውመውታል።
የኮንደስተር ሲችዋሌ አለባበስ ምንም ስህተት የለውም ሲሉም ፓርላማው ይቅርታ እንዲጠይቅ እየሞገቱ ነው።
ይህ ሁኔታ በአለም ላይ ባሉ ማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ዘንድ ከፍተኛ ውግዘትን እያስተናገደ ይገኛል። በርካታ ወንዶች የሴቶችን አለባበስ ለመቆጣጣር እንደሚፈልጉ ፍንትው ያለ ማሳያ ነው ብለዋል።












