በቤልጂየም አንዲት ታዳጊን ደፍረው ለሞት የዳረጉ አምስት ወንዶች ተያዙ

የፎቶው ባለመብት, AFP
በቤልጂየም የ14 አመቷን ታዳጊ በቡድን ደፍረው ለሞት ዳርገዋል የተባሉ አምስት ታዳጊ ወንዶች በቁጥጥር ስር ዋሉ።
ታዳጊዋ ከአራት ቀናት በኋላ ራሷን አጥፍታለች።
የቤልጂየም ሚዲያዎች ሪፖርት እንዳደረጉት ጥቃቱ ሲደርስባት የሚያሳዩ ምስሎች በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች እየተጋሩ ነበር ብለዋል።
የአገሪቱ አቃቤ ህግ እንዳሳወቀው ሶስቱ ተጠርጣሪዎች ከ18 አመት በታች ሲሆኑ ሁለቱ ግን 18ና 19 መሆናቸውን አስታውቆ በዛሬውም እለት ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ብሏል።
ታዳጊዋ መሞቷን ተከትሎ በቁጥጥር ስር የዋሉት ታዳጊዎች ምርመራ እንደተከፈተባቸውም ተዘግቧል።
የቤልጂየም ሚዲያ ሪፖርት እንዳደረገው ታዳጊዋ አንድ ጓደኛዋን መቃብር ስፍራ አካባቢ ሊገናኙ ቀጠሮ ይዘው የነበረ ቢሆንም አራት ጓደኞቹን ይዞ መጥቶ በቡድን ደፍረዋታል።
ጥቃት ሲደርስባት የሚያሳዩ ምስሎችም በማህበራዊ ሚዲያዎች ተጋርተዋል።
"በእነዚህ ምስሎች ናቸው አለም ሁሉ ያያት፤ ሙሉ አለሟ ተገለባበጠ" በማለት አባትዋ ሄት ኒውስባልድ ለተባለ የቤልጂየም ሚዲያ ተናግሯል።
ጉዳዩ የቤልጂየም ባለስልጣናትን አስቆጥቷል የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳራ ሺልትዝ ወሲባዊ ጥቃቶችን የሚያሳዩ ምስሎች በበይነ መረብ እንዳይጋሩ ለማድረግ ጠንከር ያለ እርምጃ እንደሚወስዱ ቃል ገብተዋል።
"እንዲህ አይነት ጥቃቶችን የሚያሳዩ ምስሎች በማህበራዊ ሚዲያ መጋራት የሚረብሽ ብቻ ሳይሆን ህገ ወይም ነው። በጭራሽ መደረግ የሌለበት ነገር ነው" ያሉት ሚኒስትሯ ቡድንም አዋቅረው ከተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያዎች ተወካዮች ጋር ለመነጋጋርና ቁጥጥር የሚደረግበትን ፖሊሲም አንደሚገመግሙ አስታውቀዋል።
"በጭራሽ ቃላት የለኝም። አፀያፊ ነው" በማለት የቤልጂየም ፍትህ ሚኒስትር ቪንሰንት ቫን ኩይኬንቦርን በትዊተር ገፃቸው አስፍረዋል።
"ወሲባዊ ጥቃት የደረሰባችሁ እባካችሁ ሪፖርት አድርጉ። ፍትህ ከናንተ ጎን ናት። ጥቃት ያደረሱባችሁን ለመቅጣት ሁሉንም ነገር እናደርጋለን። እንዲሁም እንዲህ አይነት ምስል የሚያጋሩትንም ጭምር" ብለዋል።
ሊዝቤት ስቲቨንስ የተባሉ የስርዓተ ፆታ ባለሙያ ለቪአርቲ ሚዲያ እንደተናገሩት ይህ ጥቃት ብቸኛ እንዳልሆነና በቤልጂየም በየአመቱ 200 የቡድን ደፈራዎች ሪፖርት ይደረጋሉ ብለዋል።












