ተቃዋሚዎች "ቧልት" ባሉት ምርጫ የሶሪያው ባሻር አል አሳድ አሸነፉ

ታትሟል

የሶሪያው ፕሬዝዳንት በሽር አል አሳድ አገር አቀፍ ምርጫ ተካሄዶ በከፍተኛ ድምጽ ማሸነፋቸውን ተነገረ።

በዚህም መሠረት አገሪቱን ለአራተኛ የሥልጣን ዘመን ይመራሉ።

አሳድ አሸነፉ የተባለበት የምርጫ መቶኛ ምጣኔ 95.1 በመቶ የመራጮችን ድምጽ በማግኘት ነው ተብሏል።

ተቀናቃኛቸው ሆነው የቀረቡት አብዱላ ሳሉም አብዱላ እና መሐመድ አህመድ ማሪ በድምሩ የመራጩን 4 ከመቶ እንኳ ያልሞላ ድምጽ በማግኘት ተሸንፈዋል ተብሏል።

የሶሪያው አል አሳድ ዋንኛ ተቃናቃኞች ምርጫውን "ቧልት" ሲሉ ያጣጣሉት ሲሆን የአውሮፓ ኅብረትና አሜሪካም ምርጫው ነጻና ፍትሐዊ ያልነበረ ነው ብለዋል።

አሳድ ድምጽ በሰጡበት ረቡዕ ዕለት ለጋዜጠኞች ሲናገሩ "ምዕራቡ ዓለም ስለእኛ ምርጫ የሚናገረው ገለባ ነው፤ ዋጋም አንሰጠውም" ብለዋል፡፡

ከዓመታት በፊት በመጋቢት 2011 (እአአ)በሶሪያ የተጀመረውን የሕዝብ ተቃውሞ ተከትሎ አሳድ በወሰዱት እርምጃ አገሪቱ ለድፍን አሥር ዓመት እልቂትና ጦርነት፣ ስቃይና ዋይታ አልተለያትም።

በዚህ የሶሪያ ጦርነት ወደ 400ሺህ የሚጠጉ ዜጎች ሲሞቱ 6 ሚሊዮን ዜጎች ውድ አገራቸውን ጥለው ተሰደዋል፡፡

ይህ የአሁኑ ምርጫ የተካሄደው መንግሥት የአስተዳደር ቁጥጥር በሚያደርግባቸው ስፍራዎች ብቻ ነው፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪ በውጭ አገራት በሚገኙ የሶሪያ ኤምባሲዎችም መጠነኛ የምርጫ ሂደት ተስተውሏል።

ተቃዋሚዎች በሚስያተዳድሩት የኢድሊብ አውራጃ ምርጫውን ተቃውመው ዜጎች አደባባይ ወጥተዋል።

ባሻር አል አሳድ ከአባታቸው የወረሱትን ሥልጣን ላለፉት 21 ዓመታት ለማንም አሳልፈው አልሰጡም።

አባታቸው ሐፌዝ አል አሳድ አገሪቱን ለ25 ዓመታት አንቀጥቅጠው ከገዙ በኋላ ነበር ሥልጣን ወደ ልጃቸው የተላለፈው።

በሩሲያና በኢራን የሚደገፉት ባሻር አል አሳድ አሁን 55 ዓመታቸው ነው።