ተመራጯ ሴት ጠቅላይ ሚኒስትር ቃለ መሃላቸውን ባልተለመደ ቦታ ፈጸሙ

ፊያሜ ናኦሚ ማታኣፋ [መሃል ላይ ነጭ ለብሰው የሚታዩት] በድንኳን ውስጥ በተዘጋጀ ሥነ ሥርዓት ቃለ መሃላ ፈጽመዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ፊያሜ ናኦሚ ማታኣፋ [መሃል ላይ ነጭ ለብሰው የሚታዩት] በድንኳን ውስጥ በተዘጋጀ ሥነ ሥርዓት ቃለ መሃላ ፈጽመዋል።
ታትሟል

በደሴቲቱ አገር ሳሞዋ አዲስ የተመረጡት የመጀመሪያዋ ሴት ጠቅላይ ሚኒስትር ቃለ መሃላቸውን ባልተለመደ ቦታ መፈጸማቸው ተሰማ።

የሳሞዋ የመጀመሪያዋ ሴት ጠቅላይ ሚኒስትር 'ከሥልጣኔ አልወርድም' ባሉት ተሰናባቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ምክንያት ቃለ መሃላ እንዳይፈጽሙ ፓርላማው ተከርችሞባቸው ነበር።

በዚህም ምክንያት መሃላቸውን በፓርላማው ቅጥር ጊቢ በአትክልት ሥፍራ በተጣለ ድንኳን ውስጥ ለመፈጸም ተገደዋል።

የፓስፊክ ውቅያኖሷ ሳሞዋ ደሴትን በጠቅላይ ሚኒስትርነት ለመምራት የተመረጡት ፊያሜ ናኦሚ ማታአፋ በዚህ መልኩ ቃለ መሃላ ይፈጽሙ እንጂ አገሪቱ በማን ቁጥጥር ሥር ትሆናለች የሚል ጥርጣሬን ግን ፈጥሯል።

ለ22 ዓመታት በጠቅላይ ሚኒስትርነት በውሃ የተከበበችውን አገር የመሩት ቱይላፓ ሳሌሌ ማሊኤለጋዮይ ከሥልጣን እንዲወርዱ ፍርድ ቤት ቢያዛቸውም አሻፈረኝ ብለዋል።

የ64 ዓመቷ የቀድሞ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የአሁኗ ተመራጭ ጠቅላይ ሚኒስትር ዛሬ [ሰኞ] ቃለ መሃላ ለመፈጸም ከአገሪቱ ፓርላማ ቢደርሱም ከሥልጣን ለመውረድ አሻፈረኝ ባሉት ማሊኤለጋዮይ ሰዎች የፓርላማው በሮች ተዘግቶ ነበር የጠበቃቸው።

ከዚህ በፊት ቃለ መሃላ ወደ ሚፈጸምበት ሥፍራ እንዳይገቡ የተከለከሉት ተመራጯ ጠቅላይ ሚኒስትር ደጋፊዎቻቸው በተገኙበት በፓርላማው ቅጥር ግቢ የአትልት ሥፍራ አገራቸውን በታማኝነት ለማስተዳደር ምለዋል።

የአሸናፊዋ ጠቅላይ ሚኒስትር ፓርቲ ባወጣው መግለጫ "ዲሞክራሲ ሁልጊዜም መስፈን አለበት። ከመሠረታዊ መርሆዎች ማፈንገጥ አይገባም" ብሏል።

ሆኖም ሥልጣን አለቅም ያሉት ጠቅላይ ሚንስትር ሥርዓቱን ሕገ ወጥና ሥርዓትን ያልተከተለ ሲሉ አጣጥለውታል።

ከአንድ ወር በፊት በሳሞዋ ታሪክ ብርቱ የተባለ የምርጫ ፉክክር ከተካሄደ በኋላ ነው ይህ ሁሉ ውዝግብ የተከተለው።

ከሥልጣን ለመውረድ ያልተሰማሙት ማሌአጋዋይ የሚወክሉት ኤች አር ፒ ፒ የተሰኘው ፓርቲ ከአራት አስርተ ዓመታት በኋላ ሥልጣኑን ማስቀጠል የማይችልበት ድምጽ አግኝቶ ተመራጯ ጠቅላይ ሚኒስትር የሚወክሉት ኤፍ ኤ ኤስ ቲ ፓርቲ አሸናፊ ሆኗል።

ቀደም ብሎ በምርጫው ሁለቱም ፓርቲዎች እኩል ወንበሮችን ያሸነፉ ቢሆንም አንድ ገለልተኛ የፓርላማ አባል ድምጻቸውን ለ ኤፍ ኤ ኤስ ቲ በመስጠታቸው ነው ፓርቲው አሸናፊ መሆን የቻለው።