ሱዳን ከአሜሪካ የሽብር ደጋፊ አገራት ዝርዝር ውስጥ እንድትወጣ ተደረገ

ታትሟል

አሜሪካ ሱዳንን ለዓመታት ካቆየቻት የሽብር ተግባራትን ከሚደግፉ አገራት ዝርዝር ውስጥ እንድትወጣ የማድረግ ሂደትን ማጠናቀቋ ተነገረ።

በአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት የተዘጋጀ ሰነድ ሱዳን ከአሜሪካ የሽብር ደጋፊ አገራት ዝርዝር ውስጥ እንድትወጣ የማድረጉ ሥራ መከናወኑን አመልክቷል።

ሱዳን የሽብር ተግባራትን ከሚደግፉ የአገራት ዝርዝር ውስጥ እንድትወጣ በይፋ ውሳኔ ላይ የተደረሰው ባለፈው ታኅሣሥ ወር ላይ ሲሆን፤ የአገሪቱን ስም ሙሉ ለሙሉ ነጻ ለማድረግ የወራት ጊዜን ፈልጓል።

በዚህም መሠረት አስፈላጊው ሂደት ተጠናቆ ሱዳን ከአሜሪካ የሽብር ዝርዝር ውስጥ መውጣቷ ተግባራዊ የሆነው በዚህ ሳምንት ከዕለተ ረቡዕ ጀምሮ ነው።

ይህ ሱዳንን ለ27 ዓመታት በሽብር ደጋፊነት ያቆያት ውሳኔን ተከትሎ በአሜሪካ የተጣሉባት ማዕቀቦች በኢኮኖሚዋ ላይ ከባድ ጉዳትን አስከትሏል።

የአሁኑ የአሜሪካ ውሳኔ የሱዳንን ስም ከሽብር ጋር የነበረውን ቁርኝት የሚያላቅቅ ሲሆን በምጣኔ ሀብት በኩልም አዎንታዊ ውጤት እንደሚኖረው ተነግሯል።

አዲሱ የሱዳን አስተዳደር የአገሪቱን ስም ከሽብር ዝርዝር ውስጥ ለማስወጣት ባደረገው ጥረት ቀደም ሲል ተፈጸሙ በተባሉት የሽብር ጥቃቶች ለደረሰው ጉዳት ከፍተኛ መጠን ያለው ካሳ ለመክፈል ተስማምቷል።

የአሜሪካ እርምጃ ለሦስት አስርት ዓመታት ያህል ሱዳንን በአምባገነንነት የመሩት ኦማር ሐሰን አልበሽር ከሥልጣን ተወግደው በተመሰረተው መንግሥት ውስጥ የሲቪል ጠቅላይ ሚኒስትር ለሆኑት አብደላ ሐምዶክ እና ለአስተዳደራቸው ታላቅ ድል ነው።

ሱዳን በአሜሪካ የሽብር ደጋፊ አገራት ዝርዝር ውስጥ እንድትገባ የተደረገው ከዛሬ 28 ዓመታት በፊት ኒውዮርክ ውስጥ በሚገኘው የዓለም ንግድ ማዕከል ህንጻ ላይ የመጀመሪያ ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ ነበር።

በወቅቱ ሱዳን የአልቃኢዳ መሪ የነበረውን ኦሳማ ቢንላደንን ጨምሮ በርካታ እስላማዊ ቡድኖች በግዛቷ ውስጥ ይገኙ ነበር።