በአሜሪካ በመኪናው ውስጥ ለተገደለው ጥቁር አሜሪካዊ ፖሊስ ተጠያቂ አይሆንም ተባለ

ታትሟል

በሰሜን ካሮላይና በመኪናው ውስጥ በፖሊስ ጥይት የተገደለው ጥቁር አሜሪካዊ ጋር በተያያዘ ፖሊስ በወንጀል ተጠያቂ አይሆንም ተብሏል።

የኤሊዛቤት ከተማ ግዛት አቃቤ ህግ ለጋዜጠኞች እንዳሳወቁት አንድሪው ብራውን የተባለው የ42 አመቱን ግለሰብ ፖሊሶች የተኮሱበት መንገድ "ምክንያታዊ ነው" ብለዋል።

በያዝነው ሳምንት ማክሰኞ በነበረ ጋዜጣዊ መግለጫ አቃቤ ህግ አንድሪው ዎምበል እንዳሉት ግለሰቡ "በወቅቱ ለነበሩት ፖሊሶች ከፍተኛ የደህንነት አደጋን ደቅኖባቸው ነበር" ብለዋል። ለዚህም እንደምክንያትነት የሚያቀርቡት "በቁጥጥር ስር እንዲውል ፖሊሶች ያዘዙትን ትዕዛዝ መጣስና መኪናውንም እንደ መሳሪያ መጠቀም ነው" ብለዋል።

ባለስልጣናቶቹ እንደሚሉት ግለሰቡ መኪናውን በፍጥነት ወደ ፖሊሶች ሲነዳ ነበር ብለዋል።

የአንድሪው ብራውን ቤተሰቦች በበኩላቸው "ይህ አይን ያወጣ ግድያ ነው" ይላሉ። በትናንትናው ዕለት የነበረውን ጋዜጣዊ መግለጫ በበጎ ያላዩት የአንድሪው ብራውን ቤተሰቦች " ይህ ለቤተሰቡ ስድብና በጥፊ እንደተመታን የምንቆጥረው ነው" በማለት በጠበቃቸው በኩል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

መግለጫው እንደሚለው " መኪናው ከፖሊሶች ለመሸሽ መሞከር ብቻ ሳይሆን አራቱ ፖሊሶች ሽጉጥ አልተኮሱም። ይህም በግልፅ እንደሚያሳየው ህይወታቸው አደጋ ላይ አለመውደቁን ነው። በመጨረሻም አንድሪው የተገደለው በጭንቅላቱ ጀርባ በተተኮሰበት ጥይት ነው" በማለት ያትታል።

ቤተሰቦቹ አንድሪው ወደ ፖሊስ መኪናውን እየነዳ ነው የተተኮሰበት የሚለውን አይቀበሉትም።

አስከሬኑ ላይ የግል ምርመራ ያደረገው አካል በበኩሉ አንድሪው ምስት ጊዜ በጥይት የተመታ ሲሆን አንዱም ከጀርባ ነው ይላል።

ባለስልጣናቱ በበኩላቸው አንድሪው ሁለት ጊዜ የተተኮሰበት ሲሆን አንደኛው በትከሻው በኩልና ሁለተኛው በጭንቅላቱ ጀርባ ነው ይላሉ።

ሌሎች ጉዳቶች ከፍንጥርጣሪው ጋር የተያያዘ እንደሆነ ይናገራሉ።

ከወር በፊት የተገደለው ጥቁር አሜሪካዊ ሞት በአሜሪካ ከፖሊስ ጭካኔ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ቁጣን ቀስቅሷል።