ወልቂጤ ከነማ 'የጨዋታ መጭበርበር ነበር' በሚል ቅሬታ አቀረበ

የፎቶው ባለመብት, Wolkite City Football club Facebook
እየተገባደደ በሚገኘው በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ በድሬዳዋ ከነማ እና ፋሲል ከነማ መካከል የተደረገው ጨዋታ ተጭበርብሯል ሲል ወልቂጤ ከነማ ቅሬታውን ለእግር ኳስ ፌዴሬሽን አቀረበ።
ከትላንት በስቲያ ግንቦት 9፣ 2013 ዓ.ም በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም 9 ሰዓት ላይ በነበረው ጨዋታ የዘንድሮው የዋንጫ ባለድል ፋሲል ከነማ በድሬ ዳዋ ከነማ 3 ለ 1 ተረትቷል።
ከዚህ ጨዋታ በኋላ ወራጅ ቀጠና የሚገኘው ወልቂጤ ከነማ ጨዋታው ተጭበርብሯል ሲል ለእግር ኳስ ፌዴሬሽን ቅሬታውን አቅርቧል።
የደቡብ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጉዳዩን እንዲያጣሩለት ለሊግ አወዳዳሪው ኩባንያ እና ለእግር ኳስ ፌዴሬሽን ደብዳቤ መጻፉን ምክትል ፕሬዝዳንት ሸረፋ ደልቾ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
በሊጉ አዳማ ከነማ እና ጅማ አባጅፋር መውረዳቸው ሲታወቅ በሦስተኛነት ላለመውረድ ከሚጫወቱ ክለቦች መካከል ድሬዳዋ ከነማ፣ ወልቂጤ ከነማ እና ሲዳማ ቡና ይገኙባቸዋል።
ጨዋታው በመጭበርበሩ "ድሬ ዳዋ ከነማን ይጠቅማል፣ ወልቂጤ ከነማ ላይ ጉዳት ያደርሳል" ብለዋል ምክትል ኮሚሽነሩ።
"በ24ኛው ሳምንት ትላንት በነበረው የ9 ሰዓት ጨዋታ ላይ ድሬዳዋ ከነማ ከፋሲል ከነማ ጋር ጨዋታ ነበራቸው። በጨዋታው ፋሲል ከነማ ከአቅም በታች ተጫውቷል። የጨዋታ የማጭበርበር ሥራ ተሰርቶብኛል ብሎ ነው ወልቂጤ ከነማ ቅሬታ ያቀረበው። ይህ ደግሞ በክልሉ እግር ኳስ ፌደሬሽንም በኩል በበቂ ሁኔታ ታምኖበት የክልሉ እግር ኳስ ፌደሬሽንም ይህንን ቅሬታ ለሚመለከታቸው አካላት አቅርቧል" ብለዋል።
የክልሉ እግርኳስ ፌደሬሽን ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በጻፈው ደብዳቤ በጨዋታው ከፍተኛ የጨዋታ ማጭበርበር እንደተፈጸመ እና ይህንንም ፌደሬሽኑ ባደራጀው የቴክኒክ ኮሚቴ አካላት ሪፖርት እንደቀረበለት አስታውቋል።
"የወልቂጤ እግር ኳስ ክለብ ላይ የተፈጸመው በደል እና የጨዋታ ማጭበርበር ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ዕድገት ጸር ነው" ያለው ደብዳቤው የሚመለከታቸው አካላት አፋጣኝ የእርምት እርምጃ እንዲወስዱ ጠይቋል።
ከበፊት ጀምሮ ጨዋታዎች 'ሊጭበረበሩ ይችላሉ' የሚሉ የተወሰኑ መረጃዎች ስለነበሩ ፌደሬሽኑ የተወሰኑ ባለሙያዎችንም አሰማርቶ ሁኔታውን ይከታተለው ነበር ብለዋል።
"ቅሬታው ዛሬ ነው የቀረበው አወዳዳሪው አካልም ሆነ እግር ኳስ ፌደሬሽኑ መልስ እኛም ክለቡም ይጠብቃል" ሲሉ ገልጸዋል።
ጥያቄያቸው በዋነኝነት የጨዋታው ሂደት በገለልተኛ አካል ይገምገም የሚል መሆኑን ጠቅሰው "የጨዋታውን ሂደት የሚገመገምበት ብዙ ፓራሜትሮች ስላሉ ብዙ የሚያስቸግር አይደልም" ሲሉ አክለዋል።
ፋሲል ከነማ ቀደም ሲል የነበረው እንቅስቃሴ [ፐርፎርማንስ]፣ ያሰለፋቸው ተጫዋቾች እና አጠቃላይ የነበረውን ሂደት በገለልተኛ አካል እንዲታይ ተጠይቋል ብለዋል።
ፋሲል ዋንጫ በማንሳቱ ተጫዋቾች መቀየሩ አንዱ ግምት ሊሆን ይችላል።
"በዚህ ጨዋታ ብቻ ሳይሆን በጥቅሉ ይህ ነገር ሊፈጠር እንደሚችል ከፍተኛ ጥንቃቀቄ ለማድርግ ጥረት ሲደረግ እንደነበር እናውቃልን" ያሉት ምክትል ፕሬዝዳንቱ "ለሁሉም በሚገባ ጥብቅ መመሪያ እና ትዕዛዝ እንደተላለፈ መረጃዎች አሉ" ብለዋል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ቃል አቀባይ ባህሩ ጥላሁን በበኩላቸው ደብዳቤው እንደደረሳቸውና ቅሬታውን የመመልከት ሥልጣን ያለው ሊግ አወዳዳሪው ኩባንያ እንደሆነ ነገር ግን ከኩባንያው አቅም በላይ ከሆነ ፌዴሬሽኑ እንደሚመለከተው ገልጸዋል።
ፋሲል ከነማ 22 ጨዋታ ተጫውቶ በ52 ነጥብ ሻምፒዮን መሆኑን ባረጋገጠበት ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ኢትዮጵያ ቡና እና ሀዲያ ሆሳዕና ይከተላሉ።
የኢትዮጵያ ቡናው አቡበከር ናስር በ27 ጎሎች የሊጉን የምንግዜም ከፍተኛ አግቢነት ክብረወሰን በመስበር ጭመር ሲመራ ሙጂብ ቃሲም በ20 እንዲሁም ጌታነህ ከበደ በ12 ጎሎች ተከታዩን ደረጃ ይዘዋል።












