እግር ኳስ፡ ሌስተር ሲቲ በታሪኩ የመጀመሪያውን የኤፍ ኤ ዋንጫ አሸነፈ

Jamie Vardy

የፎቶው ባለመብት, GettyImages

የምስሉ መግለጫ, Jamie Vardy
ታትሟል

ሌስተር ሲቲ ቼልሲን በመርታት በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የኤፍ ኤ ዋንጫን አንስቷል።

ቤልጂየማዊው ዩሪ ቲለመንስ በዌምብሌይ ስታዲየም በፍጻሜው ጨዋታ የማሸነፊያዋን እና ብቸናዋን ግብ ያስቆጠረ ተጫዋች መሆን ችሏል።

ጨዋታው በግብ ሙከራዎች የታጀበና ደመቅ ያለ የነበረ ሲሆን በሁለተኛው አጋማሽ ጥሩ ሲንቀሳቀሱ የነበሩት ሌስተር ሲቲዎች 63ኛው ደቂቃ ላይ ዩሪ ቲለመንስ ከርቀት ባስቆጠራት ድንቅ ግብ የዘንድሮው የኤፍ ኤ ዋንጫ አሸናፊ መሆን ችለዋል።

ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ በተጣሉ ገደቦች ምክንያት ለወራት ከስታዲየሞች ርቀው የነበሩት ተመልካቾች በተመለሱበት ጨዋታ ሌስተሮች በታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ዋንጫውን በማንሳት ደጋፊዎቻቸውን አስፈንጥዘዋል።

21 ሺ ተመልካቾች ጨዋታውን ለመታደም በግዙፉ የዌምብሊ ስታዲየም ተገኝተዋል።

የቀበሮዎቹ ግብ ጠባቂ ካስፐር ሽማይክል ሁለት ያለቀላቸው ሙከራዎችን ባያድን ኖሮ ጨዋታው ሌላ መልክ ሊኖረው ይችል ነበር።

የሌስተር ሲቲው ተከላካይ የሁለተኛው አጋማሽ መጠናቀቂያ አካባቢ በራሱ መረብ ላይ ያስቆጠራት ግብ በቪድዮ እገዛ አማካይነት ከጨዋታ ውጪ መባሉ ደግሞ የቼልሲ ደጋፊዎችን ያስቆጨ ነበር።

ለጎሏ መቆጠር ምክንያት የነበረው የቀድሞው የሌስተር የአሁኑ የቼልሲ ተጫዋች ቤን ቺል ዌል ከጨዋታ ውጪ መሆኑ ነበር ጎሉ እንዲሻር ያደረገው።

የሌስተር ሲቲው አሰልጣኝ ብሬንዳን ሮጀርስ ደስታውን መቆጣጠር አቅቶት በግዙፉ ዌምብሌይ ስታዲየም መጨወቻ ሜዳ ላይ ተንበርክኮ ተስተውሏል።

ተጫዋቾችና ደጋፊዎችም ቢሆን ማሸነፋቸውን ማመን አቅቷቸው በደስታ እምባ ሲራጩ ነበር።

ሌስተሮች የዘንድሮውን የኤፍ ኤ ዋንጫ ማሸነፋቸው በፕሪምየር ሊጉ እስከ አራተኛ ደረጃ ይዞ ለመጨረስና በሚቀጥለው ዓመት በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ለመሳተፍ ለሚያደርጉት ጉዞ ትልቅ መነቃቃትን እንደሚፈጥርላቸው ይታሰባል።

"በጣም ደስ የሚል ስሜት ነው። እድሜ ልኬን ይህን ውድድር ስመለከተው ነው የኖርኩት። በዚህ ሰአት ደግሞ የኤፍ ኤ ካፕ ዋንጫ አሸናፊ መሆን ችያለሁ። በደንብ ዝግጁ እንደነበርን አውቃለሁ። ተጫዋቾቹ ሙሉ ዓመቱን የሚያስገርም ብቃት ሲያሳዩ ነበር። ለልፋታቸው ሽልማቱ ደግሞ ይህ ዋንጫ መሆኑ በጣም አስደስቶኛል’’ ብሏል አሰልጣኝ ብሬንዳን ሮጀርስ።

የተሸናፊው ቡድን ቼልሲ አሰልጣኝ ቶማስ ቱኽል በበኩሉ በጨዋታው ጥሩ ቢንቀሳቀሱም እድል ከእነሱ ጋር እንዳልነበረች ገልጿል። ከጨዋታ ውጭ በሚል የተሰረዘችው ግብም በጣም የምታስቆጭ እንደነበር አሰልጣኙ ገልጸዋል።

ሌስተር ሲቲዎች ከዚህ በፊት አራት ጊዜ ለኤፍ ኤ ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ ደርሰው የነበረ ቢሆንም አሸንፈው ግን አያውቁም። ዘንድሮ ግን በአምስተኛ ሙከራቸው ዋንጫውን በማንሳት በውድድሩ ታሪክ 44ኛ ክለብ መሆን ችለዋል።

አሰልጣኝ ብሬንዳን ሮጀርስ ደግሞ ከቀድሞው የማንቸስተር ዩናይትድ አሰልጣኝ ሰር አሌክስ ፈርጉሰን በመቀጠል የእንግሊዝና የስኮትላንድ ኤፍ ኤ ዋንጫ ማንሳት የቻለ አሰልጣኝ መሆን ችሏል።