ጣልያን ለመጀመሪያ ጊዜ ሴት የሰላይ አለቃ ሾመች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የቀድሞዋ አምባሳደር የጣልያን ደህንነት መሥሪያ ቤት የመጀመሪያዋ ሴት አለቃ ሆነው ተሹመዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ማሪዮ ድራጊ፤ ኤሊሳቤታ ቤሎኒ የስለላ መሥሪያ ቤቱ አለቃ ሆነው መሾማቸውን ትላንት [ረቡዕ] አስታውቀዋል።
የጣልያን ስለላ መሥሪያ ቤት 'ዲፓርትመንት ኦፍ ኢንፎርሜሽን ሴኪዩሪቲ' ይባላል። ይህ መሥሪያ ቤት የሃገሪቱን የውስጥና የውጭ ስለላ አልግሎቶች የሚቆጣጠርና ለጣልያን መንግሥት ሪፖርት የሚያደርግ ነው።
የ63 ዓመቷ ቤሎኒ የመጀመሪያዋ ሴት ተብለው ሲሾሙ ይህ የመጀመሪያቸው አይደለም።
'የጥንካሬ ተምሳሌት' ሲሉ የገለጿትን የሊግ ፓርቲ ሊቀመንበር ማቴዎ ሳልቪኒን ጨምሮ በርካታ ጣልናዊያን ፖለቲከኞች የሴትዬዋን ሹመት በፀጋ ተቀብለውታል።
በፈረንጆቹ 1958 የተወለዱት ቤሎኒ ለወንዶች ብቻ ይፈቀድ የነበረው ማሲሚሊያኖ ማሲሞ ኢኒስቲትዩት ከገቡ የመጀመሪያዎቹ ሴት ተማሪዎች መካከል አንዷ ናቸው።
የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ደራጊም የተማሩት እዚሁ ተማሪዎች ተመልምለው የሚገቡበት ትምህርት ቤት ነው።
ቤሎኒ፤ ቪዬና እና ብራቲስላቫ ውስጥ ዲፕሎማት ሆነው ካገለገሉ በኋላ ወደ ሃገራቸው ተመልሰው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ውስጥ መሥራት ጀመሩ።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መሥሪያ ቤት ውስጥ ለአራት ዓመታት ያክል የክራይሲስ ዩኒት መሪ ሆነው ሠርተዋል።
በዚህ የሥልጣን ዘመናቸው ዋነኛው ሥራቸው የነበረው በውጭ ሃገራት የተገደሉ ወይም የተጎዱ ጣልያናዊያንን ጉዳይ ማየት ነበር።
አልፎም በአፍጋኒስታንና ኢራቅ የታፈኑ የሃገራቸውን ሰዎች ጉዳይ እንዲሁም በሱናሚ አደጋ የተጎዱ ጣልያናዊያንን ሁኔታ ይከታተሉ ነበር።
ከዚህ ሥልጣናቸው በኋላ አድገው በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋና ፀሐፊ ሆነው ተሾሙ።
ይሄንን ሹመት ሲያገኙም የመጀመሪያዋ ሴት ጣልያናዊት ነበሩ።












