አሜሪካ: በዕጣ 12 ሰዎች በሚለዩበት የአሜሪካ ጎሽ ግድያ ለመሳተፍ 45 ሺህ ሰዎች ተመዘገቡ

ቢሶን የተሰኘው አሜሪካ ውስጥ የሚገኝ የጎሽ ዝርያ

የፎቶው ባለመብት, GETTY IMAGES

የምስሉ መግለጫ, ቢሶን የተሰኘው አሜሪካ ውስጥ የሚገኝ የጎሽ ዝርያ
ታትሟል

በግራንድ ካንየን ቁጥራቸው በከፍተኛ ደረጃ የጨመረውን ቢሶን የተባሉ እንስሳቶችን ለመቆጣጠር የአሜሪካ ብሔራዊ ፓርክ አገልግሎት (ኤንፒኤስ) የበጎ ፈቃደኞችን እገዛ መጠየቁን ተከትሎ ከ 45,000 በላይ ሰዎች ተመዝግበዋል፡፡

ቢሶን የአሜሪካ ጎሽ ተብሎም ይጠራል።

ቁጥሩ መጨመሩን ተከትሎ አካባቢ ላይ ጉዳት ያደርሳል በሚል መንጋውን ለመቀነስ ስመ ገናናው የአሪዞና ብሔራዊ ፓርክ 12 "የተካኑ በጎ ፈቃደኞችን" እፈልጋለሁ ብሏል፡፡

በአሜሪካ ብሔራዊ ፓርኮች አደን በመከልከሉ ዝግጅቱ “አደን” ተብሎ አልተመደበም፡፡

እርምጃው አደገኛ ውጤት ሊያስከትል ይችላል በሚል አንዳንድ የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያዎች አስጠንቅቀዋል፡፡

ሎተሪው ሰኞ ዕለት ተከፍቶ ከ48 ሰዓታት በኋላ 45,040 አመልካቾች አግኝቷል፡፡

በቅድሚያ 25 ሰዎች ይመረጣሉ። ከእነዚህ 'ዕደለኞች' መካከል በአደንና እና በሌሎችም ችሎታዎች 12 ሰዎች ተለይተው በሰሜናዊ የፓርኩ ሪም አካባቢ ቢሶንን የመግደል ዕድል ይሰጣቸዋል፡፡

በኤንፒኤስ ሕግ መሠረት በጎ ፈቃደኞች አንድ ድጋፍ ሰጪ ሠራተኛ እንዲኖራቸው ተፈቅዷል። ቢሶን ከ900 ኪሎ ግራም በላይ ሊመዝን ይችላል።

አልሞ-ተኳሾቹ ማንኛውንም ስጋ የሚያጓጉዙት በሸክም ሲሆን በሞተር ተሽከርካሪ ወይም በዕቃ ጫኝ እንስሳት መጠቀም አትችሉም ተብለዋል።

ዝግጅቱ ለጉዞ በማያመች ድንጋያማ እና አንዳንድ ጊዜም በረዶ ባለበት አካባቢ ሲሆን ከፍታውም ከ 2,440 ሜትር በላይ ይሆናል፡፡

መንጋው በቅርብ ዓመታት በፍጥነት አድጎ 600 ቢሶንበመድረሱ የሙከራ ፕሮግራሙ ማስፈለጉን ባለሥልጣኖቹ ይናገራሉ፡፡

የአርኪዮሎጂ ሥፍራዎችን ለማስቀረት፣ የአፈር መሸርሸር እና የውሃ ብክለትን ለመቀነስ የመንጋውን ቁጥር ወደ 200 ያህል እንደሚቀንሰው ተስፋ ተደርጓል፡፡

በአደን ምክንያት በ19 ኛው ክፍለ ዘመን ለመጥፋት ከመቃረቡ በፊት ቢሶን በአብዛኞቹ የአሜሪካ አካባቢዎች ይኖር ነበር።

ከ30 እስከ 60 ሚሊዮን የሚገመተው የቢሶን ቁጥር በ1800ዎቹ መገባደጃ ወደ 400 ቀንሷል፡፡