ከሟቹ ፕሬዝዳንት ጋር አታነፃፅሩኝ ሲሉ የታንዛኒያዋ መሪ ጠየቁ

ፕሬዝደንት ሳሚያ ሱሉሁ ሃሰን

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝደንት ሳሚያ ሱሉሁ ሃሰን
ታትሟል

ከሟቹ ፕሬዝዳንት ጆን ማጉፉሊ ጋር አታነፃፅሩኝ ሲሉ የታንዛኒያዋ መሪ ጠየቁ።

የጆን ማጉፉሊን ሞት ተክትሎ የታንዛኒያ ፕሬዝዳንት ሆነው የተሾሙት ሳሚያ ሱሉሁ ሃሰን የህዝብ እንደራሴዎች እርሳቸውን ከሟቹ ፕሬዘዳንት ማጉፉሊ ጋር በማነጻጸር የሚያደርጉትን ክርክር እንዲያቆሙ ጠይቀዋል።

ፕሬዝዳንቷ ምክር ቤቱ በመንግሥት አጀንዳ ላይ ማተኮሩን ትቶ እርሳቸውን ከቀድሞ ፕሬዝዳንት ጋር በማነፃፀር በመጠመዱ መበሳጨታቸውን ገልፀዋል።

ታንዛኒያን በአዲስ መንገድ ለመምራት ባላቸው ቁርጠኝነት እየተወደሱ ያሉት ፕሬዝዳንቷ፤ እሳቸው እና ሟቹ ፕሬዝዳንት "አንድ እንደነበሩ" በመግለፅ ማጉፉሊ የጀመሩትን ስራ ማስቀጠል ላይ ማተኮራቸውን ገልፀዋል።

"በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሚሽከረከር ጉዳይ የምክር ቤቱን ክርክር እየመራው መሆኑ አሳስቦኛል" ሲሉም ገልፀዋል።

"በመንግሥት በጀት ላይ መወያየት እና እሱን ማፅደቅ ላይ ማተኮር ይገባን ነበር። እስቲ ፓርላማው ሊሰራ በሚገባው መልኩ እንስራ" ሲሉም የሃይማኖት አባቶች ባዘጋጁት ብሔራዊ ኮንፈረንስ ላይ ተናግረዋል።

ጉባኤው ለሟቹ ፕሬዘዳንት መታሰቢያ እና ለአዲሶቹ መሪዎችም ለመፀለይ ታስቦ የተዘጋጀ ነበር።

አዲሷ ፕሬዝዳንት በኮሮናቫይረስ ዙሪያ የሚያማክራቸውን ግብረ ኃይል ያቋቋሙ ሲሆን ታንዛኒያዊያን የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግን ጨምሮ የተለያዩ ጥንቃቄዎችን በማድረግ የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር እንዲያግዙ ጠይቀዋል።

ሳሚያ የታነዛኒያ የመጀመሪያዋ ሴት ፕሬዝዳንት ናቸው። ወደ ስልጣን ከመጡም በኋላ የተለያዩ ለውጦችን ያካሄዱ ሲሆን ይህም ተዘግተው የነበሩ መገናኛ ብዙሃንን መልሶ መክፈትን ይጨምራል።