የሰው ልጅ ህዋስን ከዝንጀሮ ሽል ጋር ማዳቀል የሞራል ክርክር አስነሳ

የሰው ልጅ በዝንጀሮ ሽል ተወግቶ

የፎቶው ባለመብት, Weizhi Ji/Kunming Univ of Science and Technology

ታትሟል

የሰው ልጅ ህዋሳትን የተሸከሙ የዝንጀሮ ሽሎች በላብራቶሪ መስራት እንደተቻለ አንድ ጥናት ይፋ አድርጓል።

አሜሪካና ቻይና የተጣመሩበት ይህ ሙከራ ከፍተኛ የሆነ የሞራል ክርክርም እንዲነሳ ምክንያት ሆኗል።

ሳይንቲስቶቹ የዝንጀሮ ሽሎቹን የሰው ህዋስ የወጓቸው ሲሆን እነዚህ ህዋሳት ወደተለያዩ የሰውነት አካላት ይሰራጫሉ ተብሏል።

እያደጉ ያሉት የሰው ህዋስን የተሸከሙት የዝንጆሮ ሸሎች ለሃያ ቀናት ጥናት ተደርጎባቸዋል።

የሰው ልጅ ለዘመናት ሰውንና እንስሳትን በማዳቀል አዲስ ፍጥረት የመፍጠር እሳቤዎች ነበሩት፤ ከነዚህም ውስጥ አንዱ በጥንታዊዋ ግሪክ ሰውና እንስሳትን በማዳቀል ለሚፈጠሩ ፍጡሮች ቺሜራ የሚል ስያሜ ሰጥተዋቸዋል።

የሳይንስና የቴክኖሎጂ ግኝቶች በላቁበት በዚህ ዘመን ሳይንቲስቶች የሰው ልጅንና እንስሳትን ማዳቀል ጀምረዋል። የሰውን ልጅ ህዋሳት በበበግና በአሳማ ሽሎች በመውጋት አዲስ ድቅሎችን ለመፍጠር ተችሏል።

በአሜሪካ ሳልክ ተብሎ በሚጠራው ተቋም ፕሮፌሰር የሆኑት ጁዋን ካርሎስ ኢዝፒሱዋ መሪነት በአውሮፓውያኑ 2017 ከሰውና ከአሳማ የተዳቀለ ፍጡር መስራት ችለዋል።

የሳይንቱስቶቹ ይህ ስራ ከፍተኛ እጥረት አለ ለሚባለው የንቅለ ተከላ ቀዶ ጥገና አገልግሎት ከመዋል በተጨማሪ የሰው ልጅ ከፅንስ ጀምሮ ያለውን አስተዳደግ በበለጠ ለመረዳትና ህመም፣ ማርጀትና ሌሎች የአካል መድከም እንዴት ይከሰታል የሚለውን ለማጥናት ይረዳል ተብሏል።

" ይህ ድቅልን መፍጠር ወይም የቺሜራ አካሄድ በባዮ ሜዲካል ዘርፍ ያሉ ምርምሮች ላይ ከፍተኛ ጥቅም ያለው ሲሆን ይህም በሰው ልጅ የመጀመሪያ እድገት ላይ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ እድሜዎች ላይ ነው" ብለዋል።

አክለውም ለህትመት የበቃው ይህ ጥናት በአሁኑ ወቅት አለ የሚባለውን የሞራል እንዲሁም ህጋዊ መመሪያዎችን አልፏል ይላሉ።

"በዋነኝነት እነዚህን ጥናቶች የምናካሂደው የሰውን ልጅ ጤና ለመረዳትና ለማሻሻል ነው" ይላሉ።

የሞራል ጥያቄዎች

የሰውና የእንስሳን ህዋስ ማዳቀል በሚደረጉ የምርምር ዘርፍ ላይ ይህ የመጀመሪያ ሙከራ አይደለም፤ እሳቸውና ሌሎች ተመራማሪዎች ከዚህ ቀደም የሰው ልጅ ህዋስን በአይጥ፣ በአሳማና በበግ ሺሎች ላይ ማሳደግ ችለዋል።

የሳይንቲስቶቹ ዋነኛ አላማ እንደ ጣፊያ የመሳሰሉትን በከፍተኛ ደረጃ እጥረት የሚከሰትባቸው የሰው ልጅ አካላት በእንስሳት ውስጥ በመፍጠርና በማሳደግ ለንቅለ ተከላ ማዘጋጀት ነው።

ምርምሩ የሞራል ጥያቄዎችንም በማስነሳት ላይ ነው፤ ዋነኛውም አንገብጋቢ ጉዳይ የሰው ልጅ ህዋስን እንስሳት ውስጥ ካስገባነው በእንስሳት አእምሮ ውስጥ በመገኘት ልክ እንደሰው ልጅ አመዛዛኝ ሁኔታ ሊያላብሳቸው ይችላል የሚል ነው።