ትንሿ የአፍሪካ ቀንድ ግዛት ሶማሊላንድ ለምን ቻይናን አስቆጣች?

ታትሟል

ታይዋን እና ሶማሊላንድ ምንም እንኳን ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እውቅና ባይሰጣቸውም ሁለቱም እራሳቸውን እንደ ሉአላዊ አገር ማወጅ ከጀመሩ ሰነባብተዋል። ሁለቱም ደግሞ የቀረበ ግንኙነት አላቸው።

"እንኳን ወደ ቢሯችን መጣችሁ'' ሲሉ የቢቢሲን ዘጋቢ የተቀበሉት በሶማሊላንድ የታይዋን ዲፕሎማቲክ ሚሽን ሦስተኛ ፀሐፊ የሆኑት ቹዋ ሹዎ ናቸው።

ጽህፈት ቤታቸው የሚገኘው በሶማሊላንድ ዋና ከተማ ሃርጌሳ ውስጥ የሐይማኖት ጉዳዮች ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ግቢ ውስጥ ነው ያለው።

መሀል ላይ ቀይ፣ ነጭ እና ሰማያዊ ቀለም ያለው የታይዋን ባንዲራ ይውለበለባል።

ምናልባት በርካቶች የታይዋን እና የሶማሊላንድን ግንኙነት ግራ የሚያጋ አድርገው ሊያስቡት ይችሉ ይሆናል፤ ነገር ግን ሁለቱ አገራት በብዙ ነገሮች የሚመሳሰሉበት ነገር አለ።

ዋነኛው ደግሞ ታይዋን ቻይናን ሶማሊላንድ ደግሞ ሶማሊያን ማበሳጨታቸው ነው።

ሁለቱም አገራት በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ እንደ ሉአላዊ አገር አውቅና ያልተሰጣቸው ሲሆን ሁለቱም ትልልቅ ጎረቤቶች አሏቸው። ሁለቱም ጎረቤቶቻቸው (ቻይና እና ሶማሊያ) የግዛታቸው አካል አድርገው ነው የሚቆጥሯቸው።

ሶማሊላንድ እና ታይዋን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የመሰረቱት ባሳለፍነው ዓመት ሲሆን፤ በዚህ እርምጃ ሁለቱም ጎረቤቶቻቸው ደስተኛ አለመሆናቸውን በተደጋጋሚ ገልጸዋል።

ታይዋን ከሶማሊላንድ ጋር ግንኙነት መጀመሯን ተከትሎ ሶማሊያ ታይዋንን የወቀሰች ሲሆን፤ ቻይና በበኩሏ ኃላፊዎች ወደ ሶማሊላንድ በመላክ ከታይዋን ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንዲያቋርጡ ጠይቃለች።

ቻይና ታይዋን ከሶማሊላንድ ጋር የመሰረተችው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በባሕርና በምድር ከእሲያ፣ መካከለኛው ምሥራቅና ከአፍሪካ ጋር የንግድ ትስስር ለመፍጠር የዘረጋቸው 'የቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ' ላይ ተጽህኖ ሊፈጥር ይችላል የሚል ስጋት እንዳለባት ይገመታል።

እጅግ በጣም ወሳኝ የሆነው የበርበራ ወደብ በሶማሊላንድ የሚገኝ ሲሆን አገሪቱ ከቻይና ነጻነቷን ለማወጅ ከምትጥረው ታይዋን ጋር ግንኙነት መመስረቷ ምናልባትም በቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩ አይቀርም።

"ሶማሊላንድ የታይዋን የምሥራቅ አፍሪካ በር ናት፥። እዚህ ሆኜ 10 የምሥራቅ አፍሪካ አገራትን እወክላለው" ይላሉ በሶማሊላንድ የታይዋን ተወካይ የሆኑት አለን ቼንዋ።

ከዚህ በተጨማሪ ቻይና በቅርቡ የሶማሊላንድ ሌላኛዋ ጎረቤት በሆነችው ጂቡቲ በታሪኳ ለማጀመሪያ ጊዜ ወታደራዊ ካምፕ መስርታለች። ታይዋን ሶማሊላንድ አካባቢ እንቅስቃሴ ማድረግ ከጀመረች ደግሞ ለቻይና ይህ ትልቅ ስጋት ነው።

ታይዋን ደግሞ ወደ ነጻናት በምታደርገው ጉዞ ሶማሊላንድን ዋነኛ አጋሯ አደርጋ ይዛታለች።

"ሶማሊላንድ የታይዋን የምሥራቅ አፍሪካ በር ናት፥። እዚህ ሆኜ 10 የምሥራቅ አፍሪካ አገራትን እወክላለሁ። ኬንያ እና ኢትዮጵያን ጨምሮ ማለት ነው" ይላሉ አለን ቼንዋ።

አፍሪካ ውስጥ ከሶማሊላንድ በተጨማሪ ኢስዋቲኒ ብቻ ናት ከታይዋን ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላት። ግንኙነታቸውም በአውሮፓውያኑ 1968 ጀምሮ የተመሰረት ነው።

በሶማሊላንድ የታይዋን ዲፕሎማቲክ ሚሽን ሦስተኛ ፀሐፊ የሆኑት ቹዋ ሹዎ የሁለቱ አገራት ግንኙነት ጥቅሙ ለሁለቱም ከፍተኛ እንደሆነ ይገልጻሉ።

ታይዋን በግብርና፣ በቴክኖሎጂ፣ በትምህርት፣ በጤና አገልግሎት፣ በምርጫ እና በኃይል ላይ ለሶማሊላንድ ድጋፍ ታደርጋለች። ሶማሊላንድ ደግሞ ተፈጥሮአዊ አቀማመጧ ወሳኝ መሆኑ፣ ከፍተኛ የአሳ ምርት መኖሩ፣ የተፈጥሮ እና የቱሪዝም ሀብቷም ከፍተኛ መሆኑ ለታይዋን ከፍተኛ ጥቅም አለው።

"ሶማሊላንድ ታይዋንን ታላቅ ወንድሜ እያለች ነው የምትጠራው" ይላሉ ቹዋ ሎዎ። "ነገር ግን ግንኙነታችን በጋራ መርህ እና ትብብር ላይ የተመሰረት እንደሆነ ማሰብ እፈልጋለው። ሁሌም ቢሆን ከሶማሊላንድ ጎን መሆን ነው የምንፈልገው" ብለዋል።

"በአሁኑ ጊዜ በፍጥነት ነጻነታችን ማወጅ አንፈልግም፤ ምክንያቱም እኛ ከመጀመሪያውም ነጻነታችንን አውጀናል። ሁለታችንም የሚያስፈልገን ዓለም አቀፋዊ እውቅና ብቻ ነው። ሁለታችንም ይህንን አስቸጋሪ ሁኔታ እንጋራዋለን።"

ነገር ግን ሁሉም ሶማሊላንዳውያን በሁለቱ አገራት መካከል በተፈጠረው ግንኙነት ደስተኞች አይደሉም። አንዳንዶች የቻይናን ወዳጅነት ማጣት የሚያስከትለው ጉዳት ከታይዋን ከሚገኘው ጥቅም አይበልጥም ይላሉ።

"ሁለት እርቃናቸውን የሆኑ ሰዎች እርስ በርስ ሊረዳዱ አይችሉም። ታይዋን ከምታስፈልገን በላይ ታላቋ ቻይና በእጅጉ ታስፈልገናለች" ብለዋል የከብት ነጋዴው ኢስማኤል ሞሐመድ።

ሌላኛዋ ነጋዴ ሙና አደንም ብትሆን ብዙ ጥርጣሬዎች አሏት።

"ከታይዋን ጋር የተጀመረው ግንኙነት የሶማሊላንድ መሪዎች ወደ እብደት ውስጥ መግባታቸውን የሚያሳይ ነው" ትላለች።

"መጀመሪያ ላይ ሶማሊላንድ ከታይዋን ጋር ግንኙነት ስትመሰርት ቻይናን ለማስቀናትና ትኩረቷን ወደ ሶማሊላንድ እንድታደርግ ታስቦ ነበር የመሰለኝ። ግንኙነታቸው አሁንም ድረስ መቀጠሉ አሳሳቢ ነው።"

ነገር ግን አሁንም ቢሆን የሶማሊላንድ ባለስልጣናት ወደኋላ የሚሉ አይመስልም። ጊዜያዊ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሊባን ዩሱፍ ኦስማን "ሁለቱ ግዛቶች ተመሳሳይ የሆነ የዴሞክራሲ እና የነጻነት እሴቶችን ይጋራሉ" ይላሉ።

"ከሶማሊላንድ ጋር ግንኙነት ለመፍጠር የሚመጣ ማንኛውንም አገር እንቀበላለን። ቻይናም ብትሆን። ነገረ ግን ለቻይና ብለን ታይዋንን አንፈልግሽም አንላትም።"

በአውሮፓውያኑ 1949 ከተጠናቀቀው የቻይና የእርስ በርስ ጦርነት በኋላ ታይዋን እና ቻይና የተለያየ መንግሥት ነው ያላቸው። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ ቤይጂንግ የደሴቷን አገር መልሳ ለመውሰድ ኃይል መጠቀም ካለባት ኃይል ለመጠቀም ዝግጁ መሆኗን አስታውቃለች።

ምንም እንኳን ታይዋን ሉአላዊነቷን የተቀበሉት ጥቂት አገራት ቢሆኑም በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠው የአገሪቱ መንግሥት ከተለያዩ አገራት ጋር የንግድና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት መፍጠር ችሏል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሊባን ዩሱፍ ኦስማንም ቢሆኑ ሶማሊላንድ ልክ እንደ ታይዋን የመሆን ተስፋ አላት ይላሉ። "የአፍሪካ ቀንድ ታይዋን መሆን እንችላለን። ታይዋን የስኬት ተምሳሌት ናት፤ እኛም ይህንኑ ታሪክ መድገም ነው የምንፈልገው።"

ሚኒስትሩ አክለውም ጥቂት የማይባሉ አገራት በዋና ከተማዋ ሃርጌሳ ቢሮዎቻቸውን እየከፈቱ እንደሆነ ይናገራሉ። ከነዚህ አገራት መካከል እንደ ኢትዮጵያ፣ ቱርክ፣ ጂቡቲ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ እና የአውሮፓ ሕብረት ተጠቃሽ ናቸው።

ልክ እንደ ታይዋን ሁሉ ሌሎች ዓለም አቀፋዊ እውቅና ያላገኙ ግዛቶችም ከሶማሊላንድ ጋር ግንኙነት መመስረት ጀምረዋል። ለምሳሌ በግብጽና ሱዳን መካከል በሚገኝ አንድ ግዛት ላይ የሚኖሩትና እራሳቸውን 'ዘ ኪንግደም ኦፍ የሎው ማውንቴን' ብለው የሚጠሩ ሰዎች ወደ ሶማሊላንድ በማቅናት ኤምባሲ መክፈት ይችሉ እንደሆነ ጠይቀዋል።

ሶማሊላንድም ብትሆን በታይዋን ዲፕሎማሲያዊ ቢሮ የከፈተች ሲሆን ቢሮውም በሞሐመድ ሃጊ ነው የሚመራው።

"እዚህ ታይፒ [የታይዋን ዋና ከተማ] ውስጥ መኖር በጣም ያስደስታል። የአየር ጸባዩ በጣም አሪፍ ነው፤ ሰዎቹም ቢሆኑ በጣም ስልጡን ናቸው። ስለአፍሪካ ከእኛ መማር ይፈልጋሉ" ሲሉ ተናግረዋል።

"ሁሌም ቢሆን ሶማሊላንድ ሶማሊያ እንዳልሆነች አስረዳቸዋለው። ሁሌም ቢሆን ሶማሊያን ከባሕር ውንብድና ጋር ስለሚያገናኙት እሱን በሙሉ አስረዳቸዋለው።"

ታይዋን ውስጥ ሦስት የሶማሊላንድ ተወላጆች ብቻ ያሉ ሲሆን አንደኛው ሞሐመድ ሃጊ ነው። ሁለት አብረውት የሚሰሩት ደግሞ ቀሪዎች ናቸው።

ነገር ግን በቅርቡ በርካታ ሰዎች እንደሚመጡ ተስፋ ያደርጋል። ምክንያቱም 20 የሚሆኑ የሶማሊላንድ ተማሪዎች በታይዋን የትምህርት እድል አግኝተው ይመጣሉ።

በታይዋን የሶማሊላንድ ተወካዩ በበኩላቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሶማሊላንድ ሲደርሱ ከባድ ግራ መገባት ገጥሟቸው እንደነበር ያስታውሳሉ።

"ሁሉም ሰው ከቻይና እንደመጣሁ ነው የሚያስበው። መንገድ ላይ በእግሬ መራመድ እወዳለው። እናም በእግሬ ስጓዝ ሁሉም ሰው 'ቻይና' 'ቻይና' እያለ ይጠራኛል። አሁን አሁን ግን ሰዎች እየተረዱ የመጡ ይመስለኛል።"

እነዚህ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰቡ ዘንድ የሉአላዊነት እውቅና ለማግኘት የሚጥሩት ሁለቱ አገራት ግንኙነት ወደፊት ለሚያስቡት ነገር ይጥቀማቸው አይጥቀማቸው ጊዜ የሚፈታው ጉዳይ ሲሆን ለአሁኑ ግን ሶማሊላንድና ታይዋንን የሚለያያቸው ያለ አይመስልም።