እግር ኳስ፡ ቲየሪ ኦንሪ በዘረኝነት ምክንያት ራሱን ከማኅበራዊ ሚዲያ አገለለ

ቲየሪ ኦንሪ
ታትሟል

የቀድሞው የአርሰልና የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን የፊት መስመር ተጫዋች ቲዬሪ ኦንሪ በተለያዩ አጋጣሚዎች የሚሰነዘሩ የዘረኝነትና ሌሎች መሰል የበይነ መረብ ጥቃቶችን በመቃወም ራሱን ከማኅበራዊ ሚዲያዎች እንዳገለለ አስታውቋል።

የ43 ዓመቱ ኦንሪ 2.3 ለሚሆኑት የትዊተር ተከታዮቹ አርብ ዕለት ባስተላለፈው መልዕክት ችግሩ በጣም አሳሳቢ እንደሆነና ችላ ለማለት እንኳን ከባድ እንደሆነ ገልጿል።

ወደ ማኅበራዊ ሚዲያዎች የሚመለሰው የማኅበራዊ ሚዲያዎች ባለቤቶች ኮፒራይት (የባለቤትነት መብት) ላይ የሚከተሉትን አይነት ጠበቅ ያለ ክትትልና እርምጃ በዘረኝነት ላይም ሲያደርጉት ብቻ እንደሆነ ገልጿል።

በጉዳዩ ላይ የተሻለ እርምጃ መወሰድ እንዲጀመርም ጠይቋል።

''በማኅበራዊ ሚዲያዎች በቀላሉ ገጽ መክፈት ይቻላል፤ ሌሎችን ማስፈራራትና የዘረኝነት መልዕክቶችን ማስተላለፍም እንዲሁ። የሚያስገርመውና የሚያሳዝነው ነገር ደግሞ እኚህ ሰዎች ማንነታቸው እንኳን በትክክል አይታወቅም'' ብሏል ፈረንሳያዊው እግረ ኳሰኛ።

''በማኅበራዊ ሚዲያዎቹ የሚታዩት ጥቃቶችና የዘረኝነት መልዕክቶቸ ችላ ለማለት እንኳን ጊዜ የሚሰጡ አይደሉም'' ብሏል።

ቲዬሪ ኦንሪ ከእንግሊዙ ክለብ አርሰናል ጋር በመሆን በፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ1999 እስከ 2007 ባሉት ዓመታት ሁለት ጊዜ የፕሪምየር ሊጉ አሸናፊ መሆን የቻለ ተጫዋች ነው።

ለአርሰናልና ለፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን በሚጫወትበት ወቅት አንዳንድ የዘረኝነት ጥቃቶች አጋጥመውት እንደነበር ባሳለፍነው መስከረም መግለጹ የሚታወስ ነው።

''እኛ ጥቃት የሚደርስብን ሰዎች ህመም ላይ እንደሆንን ሌሎች እንዲረዱ እንፈልጋለን። ሲበቃ ይበቃል'' ብሏል ኦንሪ።

አርብ ዕለት በትዊተር ገጹ ላይ ባስተላለፈው መልዕክት አክሎም ''ከነገ ጠዋት ጀምሮ እራሴን ከማኅበራዊ ሚዲያዎች አግልያለው።

ከዚህ በኋላ ወደ ማኅበራዊ ሚዲያዎች የምመለሰው የነዚህ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ባለቤቶች ልክ የኮፒራይት መብት ላይ የሚከተሉትን አይነት ጠበቅ ያለ ክትትልና እርምጃ በዘረኝነት ላይም ሲያደርጉት ብቻ ነው'' ብሏል።

''ይህ ሁኔታ እስከሚቀየር ድረስ ሁሉንም የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾቼን አጠፋቸዋለው። ለውጡ ቶሎ እንደሚመጣም ተስፋ አደርጋለው።" ብሏል።

ማኅበራዊ ሚዲያን የሚያስተዳድሩት ድርጅቶች ችግሩን ለመቆጣጠር በርካታ ሥራዎችን እያከናወኑ እንደሆነ በተደጋጋሚ ሲገልጹ ነበር።

ትዊተር በቅርቡ መሰል የማኅበራዊ ሚዲያ ጥቃቶችን ለመቆጣጠር 'ኪክ ኢት አውት' (Kick It Out) የተሰኘ አሰራር መጀመሩን አስታውቋል።

በፌስቡክ ስር የሚገኘው ኢንስታግራም በበኩሉ ባለፈው ዓመት ብቻ 6.6 ሚሊየን የጥላቻ ንግግሮችን እንዳስወገደ ገልጿል።