የብራሰልስ የቦምብ ጥቃት አድራሾች 'ለሙከራ አዛውንት ገድለዋል' ተባለ

ካሊድ (በግራ) እና ኢብራሂም ኤል-ባክሩይ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, ኢብራሂም ኤል-ባክሩይ (በቀኝ) በወንድሙ ካሊድ እርዳታ አንድ አዛውንት እንደገደለ ተገልጿል።
ታትሟል

በቤልጅየም አጥፍቶ መጥፋት የተሳተፉ ሁለት ወንድማማቾች ግድያ ምን እንደሚመስል ለማየት ቀደም ብለው አንድ አዛውንት መግደላቸውን ከቤልጅየም የወጣ ዘገባ አመለከተ፡፡

ኢብራሂም ኤል-ባክሩይ በጎርጎሮሳዊያኑ 2016 በዛቨንተም አውሮፕላን ማረፊያ በፈጸመው አጥፍቶ መጥፋት 11 ሰዎችን ገድሏል፡፡ ወንድሙ ካሊድ ደግሞ በባቡር ጣቢያ ሌሎች 20 ሰዎችን ገድሏል።

ጥንዶቹ ለጥቃት ፈጻሚዎች የ76 ዓመቱን ፖል-አንድሬ ቫንደርፐሬን መንገድ ላይ በጥይት እንደገደሉ ነግሯቸዋል ሲል ደ ሞርገን የተባለ ጋዜጣ አስነብቧል።

ቫንደርፐሬን በ 2014 ነበር የተገደሉት፡፡

እሁድ ምሽት በብራሰልስ ጄት አካባቢ በሚገኘው ካፌ የሚደግፉትን የእግር ኳስ ክለቡ አንደርሌትን በቴሌቪዥን ከተከታተሉ በኋላ ወደ ቤቱ ሲመለሱ ነበር በጥይት የተመቱት፡፡ ግድያውን በተመለከተ እንቆቅልሹ ሳይፈታ ቆይቷል።

የብራሰልስ ዓቃቤ ህጎች ግንቦት 2018 ግለሰቡን ማን እንደገደላቸው ለማወቅ ምስክሮችን ለማግኘት ቢሞክሩም በጥቅምት ወር 2020 ክሱን መዘጋታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል፡፡

የቫንደርፐሬን ሚስት ባለፈው ዓመት ወንድማማቾቹ በእርግጠኝነት ከወንጀሉ ጋር የተገናኙ መሆናቸውን በጠበቆቻቸው በኩል እንደተነገራቸው ለሞርገን ተናግረዋል፡፡ "አሁንም ድረስ ብዙ ጥያቄዎች ቢኖሩኝም አሁን ግን በተወሰነ መልኩ እፎይታ ነው" ሲሉ ተናግረዋል፡፡

'መግደል ምን እንደሚመስል ለመሞከር ነው'

ወንድማማቾቹ የግድያው ተሳታፊ ሊሆኑ መቻላቸውን የሚያሳዩ መረጃዎች የተገኙት መሐመድ አብሪኒ እና ኦሳማ ክራዬም የተባሉና በሕይወት የተረፉ ሁለት ጥቃት አድራሾች በመጠየቅ ነው፡፡

ጥንዶቹ በሚቀጥለው ዓመት ለፍርድ ከሚቀርቡ 10 ሰዎች መካከል ናቸው፡፡ በ2015 በፓሪስ ጥቃቶች ተሳትፏል ተብሎ የተከሰሰው ሳላህ አብደሰላም ከተከሳሾቹ መካከል ሌላኛው ነው፡፡

ጋዜጠኛ ዳግላስ ደ ኮኒንክ በተመለከታቸው የጽሑፍ መረጃዎች መሠረት ክራዬም የቦምቡ ፍንዳታ ከተከሰተ ከዘጠኝ ወራት በኋላ ለምርመራዎች "ካሊድ እና ኢብራሂም አንድ ሰው በመንገድ ላይ ተኩሰው እንደገደሉ ነግሮኛል" ሲል ተናግሯል፡፡

ሰኔ 2018 ደግሞ ክራዬም በመቀጠልም "ካሊድ አንድ አዛውንት ሰው እንደነበረና ሰው መግደል ምን እንደሆነ ለመሞከር እንደፈለጉ ገልጿል" ብሏል፡፡

የስዊድን ዜግነት ያለው ክራዬም የባቡር ጣቢያው ፍንዳታ ከመፈጸሙ ጥቂት ቀደም ብሎ ከካሊድ ጋር በካሜራ ታይቷል፡፡

መረጃው ሰማሁ በሚል ላይ የተመሠረተ በመሆኑና ተጠርጣሪዎቹ ስለሞቱ ጉዳዩ እንደገና ሊከፈት የሚችል አይመስልም፡፡

የብራሰልስ ዓቃቤ ህግ ቃል አቀባይ ለቢቢሲ "በግድያው ምርመራ ወቅት ጥፋተኛ የሆነውን ሰው መለየት አልቻልንም ነበር። ጥቅምት 2020 ፍርድ ቤት ጉዳዩን ለመዝጋት ወስኗል" ብለዋል፡፡

"አዲስ ማስረጃ ካለ ፋይሉን እንደገና ልንከፍተው እንችላለን። ሆኖም ግን ከዛሬ ጀምሮ ምርመራ ያልተደረገባቸው አዳዲስ አካላት የሉም፡፡"ሲል የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ጉዳዩን እየተከታተልኩ አይደለም ብሏል፡፡