ኮሮናቫይረስ፡ በብራዚል ሆስፒታሎች የኮቪድ-19ን ጫና መቋቋም ከማይችሉበት ደረጃ ደርሰዋል

ኦክስጅን የተገጠመለት ግለሰብ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

በአብዛኛዎቹ የብራዚል ትልልቅ ከተሞች የሚገኙት የጤና ተቋማት በኮቪድ -19 ምክንያት መሥራት ከማይችሉበት ደረጃ ደርሰዋል ሲሉ አንድ ተቋም አስጠነቀቀ፡፡

ይህ ፊዮክሩዝ የተሰኘው ተቋም በሪዮ ዲ ጄኔሮ የሚገኘው ተቋም እንዳለው ከብራዚል 27 ግዛቶች በ25 ቱ ዋና ከተሞች ውስጥ ከ 80 በመቶ በላይ የጽኑ ሕሙማን አልጋዎች መያዛቸውን ገልጿል፡፡

ማክሰኞ ዕለት አገሪቱ 1,972 ሰዎችን በኮቪድ-19 ምክንያት በሞት የተነጠቀች ሲሆን፣ ይህም አዲስ ክብረወሰን ሆኖ ተመዝግቧል።

ወረርሽኙ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ ብራዚል ከ 266,000 በላይ ዜጎቿን በሞት ስታጣ 11 ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ በቫይረሱ ተይዘዋል።

ከአሜሪካ በመቀጠል በአለም ከፍተኛ የሞት ቁጥር የተመዘገበባት ሁለተኛው ሃገር ስትሆን በቫይረሱ በተያዙ ሰዎች ደግሞ ሦስተኛ ሆናለች።

ሪዮ ዲ ጄኔሮን፣ ብራሲሊያን እና ሳኦ ፓውሎን ጨምሮ 15 የክልል ዋና ከተሞች ከ 90 በመቶ በላይ የጽኑ ሕሙማን ክፍል አቅማቸውን ተጠቅመዋል ብሏል ፊዮክሩዝ።

ፖርቶ አሌግሬ እና ካምፖ ግራንዴ ደግሞ ጸጽኑ ሕሙማን ክፍል አቅም ከሚችለው አልፈዋል፡፡

በሪፖርቱ መሠረት "የጤና ተቋማት ከመጠን በላይ ጫና እንዳለባቸው እና እንዲያውም መሥራት ከማይችሉበት መድረሳቸውን" ያመለክታሉ ሲል አስጠንቅቋል፡፡

ተመራማሪዎቹ ጭምብል በመልበስ እና እጃቸውን በማፅዳት አካላዊ እና ማህበራዊ ርቀትን የሚመለከቱ እርምጃዎችን የማስፋት እና የማጠናከሩን አስፈላጊነት ያጠናክራሉ ብለዋል።

ባለፈው ሳምንት ባለሙያዎች ለቫሎር ኢኮኖሚክ ጋዜጣ እንደገለጹት በቅርቡ በየዕለቱ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ2,000 በላይ ይደርሳል፡፡ ይህንን ለማስቀረት ብቸኛው መንገድ የፌደራል መንግሥቱ ቫይረሱን ለመዋጋት የአስተባባሪነቱን ሚና በመረከብ እገዳዎችን፣ የአፍና አፍንጫ ጭምብሎችን መጠቀምን እና የጅምላ ክትባትን ሲያበረታታ መሆኑን አስገንዝበዋል።

በሃገሪቱ ከስምንት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች የመጀመሪያ ዙር ክትባታቸውን ወስደዋል።

ማክሰኞ አገሪቱ ከ 70 ሺህ በላይ ቫይረሱ ያለባቸውን ሰዎች መዝግባለች። ይህም ከባለፈው ሳምንት የ 38 በመቶ ጭማሪ እንዳለው የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል። በቅርብ ጊዜ ቁጥሮቹ ከፍ ያሉት በአማዞን ማኑስ ከተማ ተገኘ ተብሎ የታሰበው በጣም ተላላፊ የቫይረስ ዝርያ በመስፋፋቱ ምክንያት ነው ተብሏል፡፡

ፕሬዝዳንት ጃየር ቦልሶናሮ ግን ቫይረሱ የሚያደርሰውን ስጋት ማቃለላቸውን ቀጥለዋል፡፡

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ በአንድ ዝግጅት ተገኝተው "እስከመቼ ስለዚህ ጉዳይ ማልቀሱን ትቀጥላላችሁ? ለምን ያህል ጊዜ በቤት ውስጥ ትቆያላችሁ? ከዚህ በኋላ ማንም ሊቋቋመው አይችልም፡፡ በሟቾቹ እናዝናለን። ሆኖም መፍትሔ ያስፈልገናል" ብለዋል።

ክልሎች የተወሰኑ እርምጃዎች ቢወስዱም ቦልሶናሮ በኢኮኖሚ ላይ የሚደርሰው ጉዳቱ ከቫይረሱ የከፋ ነው ሲሉ ውሳኔዎቹን ኮንነዋል፡፡