በካፒቶል ታጣቂ ሚሊሻ ጉዳት ሊያደርስ እንደነበር ፖሊስ ማስጠንቀቁን አሳወቀ

ታትሟል

ከወራት በፊት ነውጥ በተነሳበት ካፒቶል ሂል በቅርቡም ታጣቂ ሚሊሻ ጉዳት ሊያደርስ እንደነበር ፖሊስ መረጃ አግኝቻለሁ ብሏል።

በትናትናው ዕለት የካፒቶልን ህንፃ ጥሰው የመግባት ሴራ መወጠኑን መረጃ ደርሶኛል ፖሊስ በማለቱ አካባቢው በፀጥታ ኃይሎች ተሞልቷል።

አንድ የሚሊሻ ቡድን ማስፈራሪያ በደህንነት እንደተደረሰባቸውም ከፖሊስ የወጣው መግለጫ ያስረዳል።

የፀጥታ ኃይሎቹም " በየትኛውም የምክር ቤት አባል ላይ ሊቃጣ የሚችል ማንኛውንም ጉዳት ለመከላከል ዝግጁ ነን" ብለዋል።

ይህንንም ተከትሎ የተወካዮች ምክር ቤት ሃሙስ ዕለት ሊያደርገው የነበረውን ጉባኤ ሰርዟል።

ነገር ግን የጆ ባይደን 1.9 ትሪሊዮን የኮቪድ-19 የምጣኔ ኃብት ማዕቀፍን በተመለከተ ሴኔቱ በዚያኑ ቀን ተሰብስቧል።

የካፒቶል ፖሊስ በጉዳዩ ላይ ምን አለ?

የካፒቶል ፖሊስ ጉዳዩን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ "በካፒቶል ላይ ሊሰነዘር ይችላል የተባለውን ጥቃት ከአካባቢው፣ ከግዛቲቷና ከፌደራል አጋሮቻችን ጋር በመሆን እየሰራን ነው። የደረሰንን መረጃ እንዲህ በቀላሉ የምናየው አይደለም" ብሏል ባወጣው መግለጫ

"መረጃው ካለው ክብደት የተነሳ ዝርዝር ሁኔታዎችን በአሁኑ ወቅት ማሳወቅ አንችልም" ይላል።

ከሁለት ወራት በፊት የተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ነውጠኛ ደጋፊዎች የጆ ባይደንን የምርጫ ውጤት ለማረጋገጥ የህግ መምሪያ ምክር ቤት እንደራሴዎቹ ውይይት እያካሄዱ በነበረበት ወቅት ሰብረው በመግባት ሁከት አስነስተዋል።

በዚህም ነውጥ አንድ ፖሊስን ጨምሮ አምስት ሰዎች የተገደሉ ሲሆን የአሜሪካን ዴሞክራሲ መሰረትም የነቀነቀ ፈተና ነው ተብሏል።

በወቅቱም የካፒቶል ፖሊስ ኃላፊ ከስራቸው ለቀዋል።

የአሜሪካ የፍትህ ዘርፍ ቢሮ ለዚህ ሁከትና ነውጥ ተጠያቂ ናቸው ያላቸውን 300 ሰዎችም ከሷል። ከነዚህም መካከል የቀኝ ክንፍ አክራሪዎችና ሚሊሺያ ቡድኖች የሆኑት ዘ ኦዝ ኪፐርስና ስሪ ፐርሰንተርስ ይገኙበታል።

ዲሞክራቶቹ ነውጡ ስልጣንን በኃይል ከመቆጣጠር ጋር ያወዳደሩት ሲሆን ትራምፕም ያለመከሰስ መብታቸው እንዲገፈፍና በአመፅና ሁከት እንዲከሰሱም ለማስቻል እንደራሴዎቹ በአብላጫ ድምፅ መወሰናቸው ይታወሳል።

በስልጣን ላይ እያሉ ሁለት ጊዜ እንዲከሰሱ የተወሰነባቸው ወይም ኮንግረሱ በወንጀሎች የጠየቃቸው የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት አድርጓቸዋል። ነገር ግን ትራምፕ በሴኔቱ ነፃ ወጥተዋል።

በያዝነው ወር የካፒቶል ፖሊስ ኃላፊ ሆነው የተሾሙት ዮጋናንዳ ፒትማን ለምክር ቤቱ እንደተናገሩት ነውጡን አስነስተው የነበሩት የትራምፕ ደጋፊዎች ዋነኛ አላማ የካፒቶል ህንፃን ለማፈንዳትና የህግ መምሪያ እንደራሴ ምክር ቤት አባላትን ለመግደል ያለመ ነው ብለዋል።

"የአገር ውስጥ አሸባሪዎችን በተመለከተ የማይቋረጥ መረጃ መሰብሰብ አለብን። የባለፈው ጥቃትና ነውጥ እንዳይደገም ለማድረግ ክትትሉ መቀጠል አለበት። የትኛውም ቡድን በመሳሪያ የታገዘ ጥቃት በካፒቶል ህንፃ ላይ ቢያደርግ ሙሉ በሙሉ ተዘጋጅተናል"ብለዋል።