ሱዳንና ግብጽ የጋራ ወታደራዊ ትብብር ስምምነት ተፈራረሙ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሱዳንና ግብጽ በከፍተኛ ወታደራዊ ባለስልጣናቶቻቸው በተከታታይ ዙሮች ሲያካሂዱት የነበረውን ውይይት አጠናቀው የጋራ ወታደራዊ ትብብር ስምምነት መፈራረማቸውን ሱና ዘገበ።
የሱዳን ዜና አገልግሎት-ሱና ይህ ስምምነት የተፈረመው የግብጽ ጦር ኃይሎች ኤታማዦር ሹም ሌፍተናንት ጀነራል ሞሐመድ ፋሪድ ካርቱም ውስጥ ያደረጉት ጉብኝት ማብቂያ ላይ ነው።
የሱዳን ሠራዊት ኤታማዦር ሹም ሞሐመድ ኦስማን አል ሁሴን "ስምምነቱ ለሁለቱ አገራት ብሔራዊ ደኅንነትና በልምድ የዳበረ ጦር ሠራዊት ለመገንባት ያለመ ነው" ማለታቸውን እና ግብጽ ለሱዳን ለምታደርገውን ድጋፍ አድናቆታቸውን እንደገለጹ የቻይና ዜና ወኪል ዢንዋ ዘግቧል።
የግብጹ ከፍተኛ ወታደራዊ ባለስልጣን ሞሐመድ ፋሪድም አገራቸው ከሱዳን ጋር ያላትን ግንኙነት በሁሉም መስኮች ማጠናከር እንደምትፈልግ ገልጸው "ወታደራዊና ደኅንነት መስክ" የተለየ ትኩረታቸው መሆኑን ተናግረዋል።
ማክሰኞ ዕለት በተፈረመው የሁለቱ አገራት ወታደራዊ ስምምነት መሰረት የአገራቱ ብሔራዊ ጥቅም በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ በሚቻለው ነገር ሁሉ ተባብረው ለመስራት ከስምምነት እንደደረሱ የግብጹ አል አህራም ጋጤጣ ዘግቧል።
"የጋራ የሆኑ አካባቢያዊ ስጋቶች አሉብን፤ ስለዚህም እነዚህን ስጋቶች በሁሉም መስክ በጋራ ለመቋቋም በጋራ መስራት አለብን" ሲሉ የግብጹ ወታደራዊ ባለስልጣን ሞሐመድ ፋሪድ ተናግረዋል።
ከሁለት ቀናት በፊት የሱዳን መከላከያ ሚንስቴር የግብጽ ጦር ኃይሎች ኤታማዦር ሹሙ ወደ ካርቱም ማምራቸውን አስታውቆ፤ ኤታማዦር ሹሙ ከሱዳን ጦር ጋር ወታደራዊ ትብብር ለማድረግ ውይይቶች እንደሚደረጉ ገልጾ ነበር።
ሱዳንና ግብጽ ከዚህ ቀደም የጋራ ወታደራዊ ልምምድ ያደረጉ ሲሆን ተመሳሳይ ልምምዶች በቀጣይነት እንደሚኖሩ ይጠበቃል።
የየአገራቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት በካርቱምና በካይሮ መካከል እየተመላለሱ ውይይቶችን ሲያደርጉ መቆየታቸው የተነገረ ሲሆን አል አህራም የተባለው የግብጽ ጋዜጣ እንደዘገበው የግብጽ ፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ አልሲሲ በሐሙስና በቅዳሜ መካከል ባሉት ቀናት ውስጥ ለጉብኝት ወደ ሱዳን ይሄዳሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ግብጽ እና ሱዳን፡ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ታሸማግለን
ይህ በእንዲህ እንዳለ ግብጽ እና ሱዳን በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እንድታሸማግል ፍላጎታቸውን አሳይተዋል።
አገራቱ ይህን ያሉት የዲሞክራቲክ ኮንጎ ፕሬዝደንት ፊሊክስ ቲሼኬዲ የአፍሪካ ሕብረት የወቅቱ ሊቀመንበርነት ቦታን ከደቡብ አፍሪካው ፕሬዝደንት መረከባቸውን ተከትሎ ነው።
የሁለቱ አገራት የውጪ ጉዳይ ሚንስትሮች ባወጡት ጥምር መግለጫ የአፍሪካ ሕብረት፣ አሜሪካ፣ የአውሮፓ ሕብረት እና የተባበሩት መንግሥታት በድርድሩ እንዲሳተፉ ድጋፋቸውን ገልጸዋል።
ሚንስቴር መስሪያ ቤቶቹ በመግለጫቸው፤ ኢትዮጵያ ለሁለተኛ ዙር የግድቡን ውሃ ሙሊት የምታካሂድ ከሆነ በሁለቱ አገራት የውሃ አቅርቦት ደኅንነት ላይ ቀጥተኛ ስጋትን ይፈጥራል ብለዋል።
ሁለቱ አገራት ኢትየጵያ በአባይ ወንዝ ላይ እየገነባቸው ባለችው ኃይል ማመንጫ ግድብ ምክንያት የምናገኘው የውሃ መጠን ይቀንሳል በሚል ስጋት አላቸው። ሁለቱ አገራት በአንድ ላይ ቆመው ጥቅማቸውን የሚያስከብር አሳሪ ስምምነት እንዲፈረም ጥረት እያደረጉ ነው።
ኢትዮጵያ እየገነባችው ያለው ግድብ በወንዙ የውሃ ፍሰት ላይ ጉዳት የማስከትል መሆኑን በመግለጽ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ለማካሄድ በዝግጅት ላይ ከመሆኗ ባሻገር ብሔራዊ ጥቅሟን የማያስከበር ስምምነት ውስጥ ለመግባት ፍቃደኛ አለመሆኗን በተደጋጋሚ ስትገልጽ ቆይታለች።
በሦስቱ አገራት መካከል ያለውን አለመግባባት በውይይት ለመፍታት ለዓመታት የዘለቀ ውይይት ቢካሄድም ሁሉንም በሚያስማማ ሁኔታ ሳይቋጭ አስካሁን የቆየ ሲሆን በአፍሪካ ሕብረት አሸማጋይነት ሲካሄድ በቆየው ድርድር ግብጽና ሱዳን በአንድ ላይ በመቆም ጥቅማቸውን ለማስከበር እየጣሩ ነው።
በተጨማሪም ካለፈው ጥቅምት ወር መጨረሻ ጀምሮ ሱዳን ወታደሮቿን በማሰማራት በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያውያን አርሶ አደሮች ሰፍረውበት የነበረውንና የእራሴ ግዛት አካል ናቸው የምታላቸው ቦታዎች በቁጥጥሯ ስር ማስገባቷ ይታወሳል።
ኢትዮጵያም በሱዳን ሠራዊት ወረራ እንደተፈጸመባት በመግለጽ ወታደሮቿ ከግዛቷ እንዲወጡና የድንበሩ ጉዳይ ቀደም ሲል በተጀመረው ውይይት እንዲፈታ እየጠየቀች ትገኛለች።














