ኮሮናቫይረስ፡ የሟቾች ቁጥር 500,000 መድረሱ ‘ልብ ሰባሪ ምዕራፍ ነው’- ባይደን

ጆ ባይደን ከባለቤታቸው ጋር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

አሜሪካ በኮሮናቫይረስ ምክንያት 500,000 ዜጎቿን ማጣቷን ተከትሎ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ለህዝቡ ንግግር አድርገዋል።

"እንደ አንድ ህዝብ እንዲህ ዓይነቱን ጭካኔ የተሞላበት ዕጣ ፈንታ መቀበል አንችልም። በሀዘኑ መቆዘምን መከልከል አለብን" ብለዋል።

ፕሬዚዳንቱ፣ ምክትል ፕሬዚዳንቱ እና የትዳር አጋሮቻቸው ከንግግሩ በኋላ በኋይት ሃውስ በነበረው የሻማ ማብራት ሥነ-ስርዓት ወቅት የህሊና ፀሎት አድርገዋል፡፡

አሜሪካ ከ 28.1 ሚሊዮን በላይ ዜጎቿ በቫይረሱ በመያዛቸውም በዓለም አቀፍ ደረጃ ቀዳሚ ሆናለች።

ፕሬዝዳንቱ "ዛሬ ሁሉም አሜሪካውያን እንዲያስታውሱ እጠይቃለሁ፡፡ ያጣናቸውን እና ወደ ኋላ የተውናቸውን ዳግም አስታውሱ" ሲሉ አሜሪካኖች ኮቪድን በጋራ እንዲዋጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በፌደራል መንግሥቱ ሥር የሚገኙ ሁሉም ቦታዎች ላይ ለሚቀጥሉት አምስት ቀናት የአገሪቱ ሰንደቅ ዓላማ ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ ባይደን አዝዘዋል፡፡

ጆ ባይደን በኋይት ሃውስ ተገኝተው ንግግራቸውን የከፈቱት፣ በኮቪድ-19 የደረሰው አሜሪካውያን ሞት ከአንደኛው በዓለም ጦርነት፣ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት እና በቬትናም ጦርነት ከሞቱት ሰዎች ድምር ቁጥር የበለጠ መሆኑን በመጥቀስ ነው።

"ዛሬ በእውነት አስከፊ እና ልብ ሰባሪ ምዕራፍ ነው- 500,071 ሰዎች ሞተዋል" ብለዋል፡፡

በመቀጥለም "ብዙ ጊዜም እንደ ተራ አሜሪካዊ ሰዎች ሲገለጹ እንሰማለን። እንደዚህ ዓይነት ነገር የለም። ምንም ተራ ብሎ ነገር የለም፡፡ ያጣናቸው ሰዎች እጅግ የተለዩ ነበሩ፡፡ በአሜሪካ የተወለዱ ወደ አሜሪካ የተሰደዱ ናቸው" ብለዋል።

"ብዙዎቹም የመጨረሻ እስትንፋሳቸውን በአሜሪካ ወስደዋል" ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ጆ ባይደን ሚስታቸው እና ሴት ልጃቸው በጎርጎሮሳዊያኑ 1972 በመኪና አደጋ የተገደሉ ሲሆን ወንድ ልጃቸው ደግሞ በ 2015 በካንሰር ህይወቱ ማለፉን በማንሳት የራሳቸውንም የሃዘን ተሞክሮ ጠቅሰዋል።

"ለእኔ በሀዘን ውስጥ ያለው መንገድ ዓላማን መፈለግ ነው" ብለዋል።

ባይደን በወረርሽኙ ላይ የወሰዱት እርምጃ ከቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የተለየ ነው። ትራምፕ በአደገኛው ቫይረስ ተጽዕኖ ላይ ጥርጣሬ ያሳደሩ እና የቫይረሱ ስርጭትን ለመከላከል ጭምብሎችን መልበስ እና ሌሎች እርምጃዎችን ፖለቲካዊ አድርገውት እንደነበር ይነገራል፡፡

በኮሮናቫይረስ የሞተ የቤተሰብ አባሏን ስትሰናበት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ባይደን ስልጣኑን ከመረከባቸው ከአንድ ቀን በፊት 400,000 አሜሪካውያን በቫይረሱ ምከንያት የሞቱበትን ክስተት አስበው ውለዋል፡፡

በሌላ በኩል በዋሽንግተን በብሔራዊ ካቴድራል ደወሎች 500 ጊዜ ተደውሏል- በወረርሽኙ ህይወታቸው ላለፈው ለአንድ ሺህ አሜሪካዊ አንድ ጊዜ ማለት ነው፡፡

በአሜሪካ ምን እየሆነ ነው?

በኮሮቫይረስቫይረስ የተያዙት አሜሪካውያን ቁጥር በሁለተኛ ደረጃ ከያዘች ህንድ (11 ሚሊዮን) እና ብራዚል (10.1 ሚሊዮን) ጋር ሲነፃፀር በእጥፍ የሚበልጥ ነው፡፡ ብራዚል በ 244,000 የሟቾችን ቁጥር ሁለተኛ ስትሆን ሜክሲኮ 178,000 ሰዎችን አጥታ በሦስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡

"ከአስርተ ዓመታት በኋላ በመተንፈሻ አካላት ኢንፌክሽን ምክንያት የደረሰውን የብዙዎች ሞት በሃገሪቱ ታሪክ ውስጥ እንደ ታላቅ ታሪካዊ ምዕራፍ ይገልጹታል" ሲሉ የበሽታ መከላከያ ባለሙያው ዶ/ር አንቶኒ ፋውቺ ለሲ.ኤን.ኤን ገልጸዋል።

"አስገራሚ ቁጥር ነው። ከአንድ ዓመት በፊት ግማሽ ሚሊዮን አሜሪካውያን በዚህ በሽታ ሕይወታቸውን ያጣሉ የሚል ግምት አልነበረኝም" ብለዋል በብራውን ዩኒቨርሲቲ የኅብረተሰብ ጤና ትምህርት ቤት ዲን የሆኑት ዶ/ር አሺሽ ጅሃ።

"በዚህች ሀገር ውስጥ ብዙ አቅም፣ ብዙ ሀብት አለን ... የምንከላከለው ስለነበር መከሰት አልነበረበትም፡፡ አሁን እዚህ ደርሰናል፡፡ የምንሰጠው ምላሽ የተሳሳተባቸውን መንገዶች ሁሉ ማንፀባረቅ ያለብን ይመስለኛል" ሲሉ ለቢቢሲ ገልጸዋል፡፡

የዋሽንግተን ዩኒቨርስቲ ከሰሞኑ ይፋ ባደረገው ትንበያ መሠረት ቢያንስ 90,000 የሚሆኑ ተጨማሪ አሜሪካውያን እስከ ሰኔ 1 ቀን ድረስ በቫይረሱ ይሞታሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በግምቱ መሠረት በግንቦት መጨረሻ ቫይረሱ በየቀኑ 500 ገደማ አሜሪካውያንን እንደሚገድል ይገምታል። በአሁኑ ወቅት በየቀኑ ወደ 2,000 የሚጠጉ ሰዎች በቫይረሱ እንደሚሞቱ ይገመታል።

በየቀኑ ወደ 1.6 ሚሊዮን የሚጠጋ ክትባት ለአሜሪካዊያን እየተሰጠ በመሆኑ ሆስፒታል የሚገቡ ሰዎች መጠን ለ40ኛ ተከታታይ ቀናት ቀንሷል፡፡ ሆኖም ባለሙያዎች በአገሪቱ ውስጥ እየጨመረ በሄደው አዲስ የኮሮናቫይረስ ዝርያ የሟቾችን ቁጥር ሊጨምር ይችላል በሚል አሳስቧቸዋል፡፡

አኃዞች ቢሻሻሉም በኮሮናቫይረስ ምክንያት የአሜሪካኖች በሕይወት የመኖር ዕድሜን በአንድ ዓመት ቀንሷል ሲል የአሜሪካ የበሽታ መቆጣጠርና መከላከል ማዕከል ባለፈው ሳምንት አስታውቋል፡፡ በቫይረሱ እጅግ በተጎዱትና በቁጥር አናሳ በሆኑት ማህበረሰቦች ዘንድ ደግሞ ለውጡ ከፍተኛ ነው ተብሏል።

በህይወት የመኖር ዕድሜያቸው በከፍተኛ ደረጃ የቀነሰባቸው ጥቁር ወንዶች ሲሆኑ ከጥር እስከ ሰኔ 2020 ባለው ጊዜ ብቻ በሦስት ዓመት ቀንሷል፡፡

በዚህ ጊዜ ውስጥ የሂስፓኒኮች በህይወት የመኖር ዕድሜ በ 2.4 ዓመት ቀንሷል፡፡

ኮሮና
Banner