ኮሮናቫይረስ፡ ኦማን ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ10 አገራት የሚመጡ መንገደኞችን አልቀበልም አለች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኦማን ኢትዮጵያን ጨምሮ ከአስር አገራት የሚመጡ መንገደኞችን ለቀጣዮቹ 15 ቀናት በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት የተነሳ እንደማትቀበል አስታወቀች።
ኦማን እገዳ ከጣለችባቸው አስር አገራት መካከል ስምነቱ የአፍሪካ አገራት ሲሆኑ እነሱም ኢትዮጵያ፣ ሱዳን፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ናይጄሪያ፣ ታንዛኒያ፣ ጋና፣ ጊኒ እና ሴራሊዮን ይገኙባታል።
ቀሪዎቹ ሁለት አገራት ደግሞ የመካከለኛ ምሥራቅ አገሯ ሌባኖስና የደቡብ አሜሪካዋ ብራዚል ናቸው።
እንደ ኦማን የጤና ሚኒስቴር ባለሥልጣናት ከሆነ የአገሪቱ ዜጎች፣ የጤና ባለሙያዎች፣ ዲፕሎማቶች እና ቤተሰቦቻቸው ብቻ ከእነዚህ አገራት የሚመጡ ከሆነ እንዲገቡ ይፈቀድላቸዋል።
ኦማን እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰችው በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ከምሥራቅ አፍሪካ ወደ አገሯ ከገቡ መንገደኞች መካከል 18 በመቶ ያህሉ በኮሮናቫይረስ ተይዘው በመገኘታቸው ነው።
ከኦማን ጋር የታሪክ እና የባህል ትስስር ላላቸው አገራት ይህ ውሳኔ አስደንጋጭ ነው ተብሏል።
ዕገዳው ከተጣለባቸው መካከል የምትገኘው ታንዛኒያ ካለፈው ዓመት ግንቦት ወር ጀምሮ አንድም በኮቪድ-19 የተያዘ ሰው በአገሯ ስለመኖሩ አላሳወቀችም።
ለበርካታ ወራት ከኮቪድ ወረርሽኝ ነጻ መሆኗን ስትናገር የቆየችው ታንዛኒያ በድንገት ባለፈው ሳምንት ፕሬዝዳንት ማጉፉሊ ሕዝባቸው ከኮቪድ-19 እንዲጠነቀቅ ምክራቸውን ለግሰዋል።
እንደ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ናይጄሪያ ያሉ አገራት ደግሞ በየዕለቱ ከፍተኛ ቁጥር ያለው በቫይረሱ የተያዘ ሰው እየመዘገቡ ነው።
እንደ ዓለም ጤና ድርጅት ከሆነ ኦማን 140,000 በኮሮና ተሕዋሲ የተያዙ ሰዎች በአገሯ መኖራቸውን በምርመራ ስታረጋግጥ ከእነዚህ መካከል 1,500 ያህሉ ሞተዋል።
በኦማን ከባለፈው ወር ጀምሮ በኮሮናቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቀስ በቀስ መጨመር እያሳየ ነው።












