በከፋ ቅዝቃዜ ወጀብ ውስጥ ባለችው ቴክሳስ ሚሊዮኖች የንፁህ ውሃ ችግር አጋጥሟቸዋል ተባለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በከፋ ቅዝቃዜ ማዕበል የተመታችው ቴክሳስ 14 ሚሊዮን የሚሆኑ ነዋሪዎች የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር አጋጥሟቸዋል ተብሏል።
ይህንንም ተከትሎ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በግዛቲቱ የከፋ አደጋ መድረሱን በማወጅ ከፍተኛ የፌደራል ገንዘብ ከዚህ ማጥ እንዲያወጣት ለማድረግ እያመቻቸቹ ነው ተብሏል።
በቅዝቃዜው ወጀብ ምክንያት ያጋጠመው የኤሌክትሪክ መቋረጥ በአንዳንድ ቦታዎች ቢመለስም የግዛቲቱ ውሃ ማከሚያ ማዕከል እክል በመግጠሙ የመጠጥ ውሃን ፈተና አድርጎታል ተብሏል።
ፕሬዚዳንት ባይደን ከሰሞኑ ቴክሳስን እንደሚጎበኙም ተናግረዋል።
የአሜሪካን ደቡባዊ ግዛቶች ያናወጠው ቅዝቃዜ የ60 ሰዎች ህይወትን ቀጥፏል ተብሏል።
የፕሬዚዳንት ባይደን አስተዳደር ከቴክሳስ በተጨማሪ፣ በኦክላሆማና ሉዚያና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጆችን አውጀዋል።
ዋይት ሃውስ ባወጣው መግለጫ መሰረት ጆ ባይደን በቅዝቃዜው ማዕበል ለተመቱ ግዛቶች የሚውል የፌደራል ድጋፍ በገንዘብ እንዲሁም በሌሎች ጉዳዮች እንዲውል ትእዛዝ አስተላልፈዋል።
"በቅዝቃዜው ማዕበል ለተመቱ ግዛቶች የሚውለው ድጋፍ ጊዜያዊ መጠለያ፣ የቤቶች ጥገና፣ በዚህ ወጀብ ንብረታቸውን ላጡና ኢንሹራንስ ለሌላቸው በዝቅተኛ ክፍያ ብድር፣ ከዚህ በተጨማሪ በዚህ አደጋ ለወደሙ የግልም ሆነ ሌሎች ንግድ ተቋማት የሚያገግሙበት መንገድ ይመቻቻል" ብሏል መግለጫው
ፕሬዚዳንት ባይደን በቴክሳስ ግዛት ትልልቅ ከሆኑት ከተሞች ሂውስተን፣ ኦስቲን፣ ዳላስ ከንቲባዎችም ጋር የፌደራል መንግሥቱ ማድረስ ስላለበት እርዳታም ተወያይተዋል ተብሏል።
ከቴክሳስ በተጨማሪ በተለያዩ የአሜሪካ ደቡባዊ ግዛቶች ከፍተኛ የውሃ እጥረት ማጋጠሙም ተነግሯል።
የቅዝቃዜ ወጀቡ ባስከተለው የውሃ መቋረጥ የጃክሰኗ ሚሲሲፒ ከተማ 150 ሺህ ነዋሪዎች የውሃ አቅርቦት የላቸውም ተብሏል። እንዲሁም በቴነሲ ትልቋ ከተማ ሜምፊስ 651 ሺህ ነዋሪዎቿ እንዲሁ የውሃ አቅርቦት ተቋርጦባቸዋል።
በአሁኑ ወቅት በጃክሰን የሚገኘው የግዛቲቱ ውሃ ማከሚያ ማዕከል መስራት መጀመሩ ቢነገርም 43 ሺህ ቤቶች የውሃ አቅርቦት እንደሌላቸው ተገልጿል።
እንዲህ አይነት ቅዝቃዜ ባልተለመደበት በርካታ የአሜሪካ ደቡባዊ ግዛቶች የበረዶ ግግሮች የውሃ መተላለፊያ ቱቦዎችን እንዳፈነዱና አንዳንድ የቤት ባለቤቶችም ብርድ ልብስ በማልበስ የውሃ ቧንቧዎችን ለማሞቅ እየሞከሩ ነው ተብሏል።
በተለይም በቴክሳስ በሶስት አስርት አመታት ውስጥ አይታ የማታውቀው ቅዝቃዜ ያጋጠማት ሲሆን ይህም ከዜሮ በታች 18 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ነው።












