በቅዝቃዜ ወጀብ ውስጥ ባለችው ቴክሳስ ነዋሪዎች ውሃ አፍልተው እንዲጠቀሙ ተነገራቸው

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአሜሪካዋ ቴክሳስ ግዛት በከፋ ቅዝቃዜ ማዕበል መመታቷን ተከትሎ ባጋጠመ የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጥ የግዛቲቱ ውሃ ማከሚያ ማዕከል እክል ገጥሞታል ተብሏል።
በዚህም የተነሳ ሰባት ሚሊዮን የሚጠጉ ነዋሪዎች ውሃ እያፈሉ እንዲጠጡ ተነግሯቸዋል።
የአሜሪካን ደቡባዊ ግዛቶች ያናወጠው ቅዝቃዜ 21 ሰዎችን ሲገድል በሚሊዮን የሚቆጠሩ ነዋሪዎችን ደግሞ የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት አልባ አድርጓቸዋል።
ግዛቲቷ በበረዶ የተሸፈነች ሲሆን፣ የበረዶ ግግሮች የውሃ መተላለፊያ ቱቦዎችን እንዳፈነዱና አንዳንድ የቤት ባለቤቶችም ብርድ ልብስ በማልበስ የውሃ ቧንቧዎችን ለማሞቅ እየሞከሩ ነው ተብሏል።
ግዛቲቱ በሶስት አስርት አመታት ውስጥ አይታ የማታውቀው ቅዝቃዜ ያጋጠማት ሲሆን ይህም ከዜሮ በታች 18 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ነው።
የግዛቲቷ የኤሌክትሪክ ኃይልም ከነዋሪው የሚቀርበውን የፍላጎት አቅርቦት ማጣጣም አልቻለም።
ከባለፈው ቅዳሜ ጀምሮ በቅዝቃዜ ውስጥ ያለችው የቴክሳስ ግዛት ላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አስተላልፈዋል።
በያዝነው ሳምንት ረቡዕ የቴክሳስ የአካባቢ ቁጥጥር ኮሚሽን ኃላፊ ቶቢ ቤከር እንዳሉት ከታከመ ንፁህ ውሃ አቅርቦት ጋር ተያይዞ 260 ሺህ ነዋሪዎች ችግር ገጥሟቸዋል ብለዋል።
የሂውስተን ከንቲባ ሲልቨስተር ተርነር የውሃ መተላለፊያ ቱቦዎች በረዶ እንዳይሰሩ ለማድረግ ነዋሪዎች ቧንቧቸውን እንዳይዘጉ ተማፅነዋል።
የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ያላቸው ውሃውን እንዲያፈሉና፣ መብራት የሌላቸው ደግሞ የታሸጉ ውሃዎችን እንዲጠጡ ጥሪ አቅርበዋል።
"የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ለቀናት ያህል በቅርቡ አይመለስም" በማለትም በጋዜጣዊ መግለጫ ላይ መናገራቸው ተዘግቧል።
ከኃይል መቋረጥና ባለው ከፍተኛ ቅዝቃዜ ምክንያት በርካቶች ብርዱን መቋቋም እንዳልቻሉና ያለ ማሞቂያ ቀናትን መቆየቱ ፈታኝ መሆኑ እየተነገረ ነው።
የተለያዩ የንግድ ተቋማትና ቤተ ክርስቲያኖች ተጋላጭ ለሆኑ ማህበረሰቦች መጠለያነት የተቀየሩ ሲሆን የታሸገ ውሃም ለነዋሪው እየታደለ መሆኑ ተገልጿል።
"በአሁኑ ወቅትም ቢሆን በቅዝቃዜ ማዕበል ላይ ነን" ብለው ያስጠነቀቁት ከንቲባው ነዋሪው ጉዞ ባያደርጉ እንደሚመከርና በተለይም በጥዋትና በማታ መጓዝ "አደገኛ ነው" ብለዋል።
የግዛቲቱ አስተዳዳሪ ግሬግ አቦት እንዳሉት እስካሁን ድረስ 1.2 ሚሊዮን ለሚሆኑ ነዋሪዎች የመብራት አገልግሎት የተመለሰ ሲሆን የሌሎችም በቅርቡ እንደሚመለስ ቃል ገብተዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ለቀናት ያህልም የተፈጥሮ ጋዝ ከግዛቲቷ እንዳይወጣ ትእዛዝ አስተላልፈዋል።












