ትራምፕ የፓርቲያቸው ሰዎች ላይ የቃላት ጦርነት ከፈቱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ነባር የሪፐብሊካን ፓርቲ አባል የሆኑት ሚች ማኮነል የተሰኙት ግለሰብ ላይ የቃላት ጦርነት ከፍተዋል።
ትራምፕ "ሚች ማለት ጨለምተኛ እና ደረቅ የፖለቲካ አጭበርባሪ ነው" ሲሉ የፓርቲያቸውን ሰው ወርፈዋል።
"ሪፐብሊካኖች ከሱ ጋር ከቆዩ ከዚህ በኋላ አያሸንፉም" ትራምፕ ሰውዬውን በማስመልከት የሰጡት አስተያየት ነው።
ሚች ማኮኔል የአሜሪካን ሰኔት ለዓመታት መርተዋል።
በቅርቡ ትራምፕ የካፒቶል ግርግርን አነሳስተዋል ተብለው ክስ እንዲመሠረትባቸው ድምፅ ሲሰጥ አይሆንም ብለው እጃቸውን አውጥተዋል።
ነገር ግን ከዚያ በኋላ ትራምፕ የካፒቶል ግርግርን በተመለከተ "የሞራል ኃላፊነት ያነሳቸው ነበሩ" ምክንያቱም ምርጫውን አስመልክቶ የሰጡት አስተያየት ውሃ አያነሳም ሲሉ የቀድሞውን ፕሬዝደንት ተችተው ነበር።
በሰኔቱ መድረክ ላይ ባደረጉት ንግግር ትራምፕ በግርግሩ ባይከሰሱ እንኳ ሥልጣን ላይ እያሉ በፈፀሟቸው ወንጀሎች ሊከሰሱ ይገባል ሲሉ ተከራክረዋል።
ትራምፕ ምን አሉ?
ትራምፕ ሥልጣን ከለቀቁ በኋላ በለቀቁት ረዥም መግለጫ ሐሳባቸውን አሰምተዋል።
"ሪፐብሊካን ፓርቲ እንደ ሚች ያሉ ሰዎችን ይዙ የቀድሞ ክብሩን ያገኛል አሊያም ጠንካራ ይሆናል ማለት ዘበት ነው" ይላል መግለጫው።
"በሚች የፖለቲካ ትንታኔ እጥረት፣ ብልህ አለመሆን እንዲሁም በባሕሪው ምክንያት ነው ሪፐብሊካኖች የሰኔት የበላይነታቸውን ያጡት" ይላሉ ትራምፕ።
ከአንድ ወር በፊት ሥልጣን የለቀቁት ትራምፕ፤ የሪፐብሊካን ፓርቲ አጋራቸው "ለምነው" ነው እንጂ በሰኔቱ መቆየት አይችሉም ነበር ይላሉ።
ትራምፕ አልፎም የሳቸው ደጋፊ የሆኑ የሪፐብሊካን ፓርቲ አባላት ላይ ሚች የሰነዘሩትን አስተያየት ነቅፈዋል።
የቀድሞው ፕሬዝደንት "አሜሪካን ቀዳሚ ለማድረግ ለሚሠሩ" የሪፐብሊካን ፓርቲ አባላት ድጋፋቸውን እንደሚቸሩ በመግለጫቸው አትተዋል።
"አቶ ማኮኔል እንደሆነ ለሃገራችን የሚበጀውን መቼም ቢሆን አያደርጉም" የትራምፕ ወቀሳ ነው።
"ቅድሚያ ለአሜሪካ የሚለው ሐሳብ እንጂ የሚች ቅዳሜ ለባለሥልጣናት አሊያም የባይደን አሜሪካ መጨረሻ የሚለው ሐሳብ አያሸንፍም።"
ትራምፕ ትዊተር ከተሰኘው ድር አምባ ላይ መወገዳቸው ተቃዋሚዎቻቸው ላይ ለሚያዘንቡት ነቀፋ የሚሆናቸው መድረክ አሳጥቷቸዋል።
ነገር ግን በሰኔቱ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ሪፐብሊካኖች መሪ የሆኑትን ሚች ማኮኔልን ለማብጠልጠል ሲሉ የለቀቁት መግለጫ ወኔያቸው እንዳልተለያቸው ማሳያ ነው።
በስምንት አንቀፆች የታጨቀው መግለጫቸው ተቀናቃኛቸውን ዴሞክራቶች ሳይሆን የገዛ ፓርቲያቸው ሪብሊካንን ያነሱ የጣሉበት ነው።
ዶናልድ ትራምፕ ሥልጣን ላይ ሳሉ ከሚች ማኮኔል ጋር የተሻለ ግንኙነት ነበራቸው።
ይህ የተቀየረው ትራምፕ በምርጫው ከተሸነፉ በኋላ ነው።
ሚች ከወርሃ ታኅሣሥ ጀምሮ ከትራምፕ ጋር አውርተው እንደማያውቁ ይናገራሉ።
በሁለቱ ሰዎች መካከል ያለው ቅራኔ የተባባሰው በፈረንጆቹ ጥር 6 በካፒቶል በተነሳውና የአምስት ሰዎችን ሕይወት በቀጠፈው ግርግር ምክንያት ነው።
ትራምፕ ግርግሩን አነሳስተዋል ተብለው እንዲከሰሱ የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ቢወስንም ሰኔቱ ግን ይህን ለማድረግ በቂ ድምፅ ሳያገኝ ቀርቷል።
ሰባት ሪፐብሊካኖች ብቻ ናቸው ከዴሞክራቶች ጋር አብረው ትራምፕ ይከሰሱ ሲሉ ድምፃቸውን የሰጡት።
ሚች ማኮኔልን ጨምሮ 42 ሪብሊካኖች ግን አይከሰሱ ሲሉ ድምፅ ሰጥተዋል።












