ኢንተር ሚላን የማንችስተር ዩናይትዱን ጄሲ ሊንጋርድ ለማስፈረም ፍላጎት እንዳለው ተነገረ

ጄሲ ሊንጋርድ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ጄሲ ሊንጋርድ
ታትሟል

በዘንድሮው የጥር የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ክለቦች የሚያተኩሩባቸውን ተጫዋቾች እየጠቀሱ ነው። ምንም እንኳ እስካሁን በዝውውሩ ስማቸው የሚነሳ ትልልቅ ተጫዋቾች ቁጥር አናሳ ቢሆንም በርከት ያሉ ተጫዋቾች ግን በዝውውሩ ክለብ የቀይራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የጣሊያኑ ክለብ ኢንተር ሚላን፤ የማንችስተር ዩናይትድና የአንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች የሆነውን የ28 ዓመቱን ጄሲ ሊንጋርድን ለመውሰድ ፍላጎት ማሳየቱን ሚረር ዘግቧል። ይህ የሚሆነው ግን ኢንተር ሚላን ዴንማርካዊው ክርስቲያን ኤሪክሰንን ካሰናበተ ነው ተብሏል።

ሌላኛውን የዩናይትዱን አማካይ ፖል ፖግባን ደግሞ የፓሪስ ሴይንት ዠርሜኑ አሰልጣኝ ማውሪሲዮ ፖቺቲኖ አጥብቀው እንደሚፈልጉት እና ቡድናቸውንም በ27 ዓመቱ ፈረንሳያዊ አማካይ ላይ መመስረት እንደሚፈልጉ ዴይሊ ስታር መረጃ ደርሶኛል ብሏል።

ሜይል እንደጻፈው ከሆነ የአር ቢ ሌፕዚጉን ፈረንሳያዊ ተከላካይ ዳዮት ኡፓሜካኖ ለማስፈረም የለንደኑ ክለብ ቼልሲ ውድድሩ ውስጥ ገብቷል። ይህንን ተጫዋች ማንችስተር ዩናይትድም እንደሚፈልገው ማንችስተር ኢቭኒንግ ኒውስ ዘግቧል።

ላለፉት ወራት ከቡድን ስብስቡ ውስጥ ያልተካተተው የአርሰናሉ አማካይ ሜሱት ኦዚል፣ ምናልባት ወደ ቱርኩ ክለብ ፌነርባቼ ሊያመራ እንደሚችል ሰን ጽፏል። የ32 ዓመቱ ኦዚል በአርሰናል ቆይታው ሊኖረው የሚችለውን 350 ሺህ ሳምንታዊ ደመወዙን ለሦስት ዓመታት ተቀናንሶ እየተከፈለው ወደ ፌነርባቼ ሊያመራ ይችላል ተብሏል።

ሌላኛው የአርሰናሉ አማካይ ሉካስ ቶሬራ ወደ ፊዮረንቲና ሊያመራ እንደሚችል የስፔኑ ሙንዶ ዲፖርቲቮ ዘግቧል። የ24 ዓመቱ ኡራጓያዊ አማካይ፣ ለስፔኑ አትሌቲኮ ማድሪድ በውሰት ተሰጥቶ እየተጫወተ ቢቆይም እንደታሰበው ስኬታማ አልሆነለትም ተብሏል።

ፉትቦል ኢንሳይደር እንደዘገበው የሊዮኑ ፈረንሳያዊ አጥቂ ሙሳ ደምበሌ ከዌስትሃም የቀረበለትን የጥር ወር ዝውውር ጥያቄ ውድቅ አድርጓል።

ከአሁን በፊት ለሴልቲክ የተጫወተው ፈረንሳያዊው አጥቂ ምናልባትም የስፔኑን አትሌቲኮ ማድሪድ ለመቀላቀል ሳይቃረብ እንዳልቀረ የስፔኑ ማርካ ጋዜጣ አስነብቧል።

ብራዚላዊው የማንችስተር ሲቲ አማካይ ፈርናንዲንሆ ከሲቲ ጋር ያለው ኮንትራት በውድድር ዓመቱ ይጠናቀቃል። በመሆኑም የ35 ዓመቱ ተጫዋች ወደ አገሩ ብራዚል ወይም ወደ ሌሎች የአውሮፓ ክለቦች ሊሄድ እንደሚችል ጎል አስነብቧል።

ቱቶ መርካቶ እንደሚለው ደግሞ ግሪካዊውን የአርሰናል የመሃል ተከላካይ ለማስፈረም ጂንዋ ከስፔኑ ሪያል ቤቲስ ብርቱ ፉክክር ይጠብቀዋል ተብሏል።

ዌስትሃም ሴኔጋላዊውን የ22 ዓመት የዋትፎርድ አጥቂ እስማየላ ሳርን ለማስፈረም 30 ሚሊዮን ፓውንድ ማዘጋጁን ሰን ሰምቻለሁ ብሏል። የዌስትሃም አለቃ ዴቪድ ሞይስ የሪያል ማድሪዱን የፊት መስመር ተሰላፊ የ27 ዓመቱን ማሪያኖ ዲያዝን በውሰት ለማምጣት ፍላጎት እንዳላቸውም ሜይል ዘግቧል።