ሄዝቦላህ በዓለም አቀፍ የዕጽ ምርትና ንግድ ውስጥ የለሁበትም አለ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የሌባኖስ ታጣቂ ቡድን ሄዝቦላህ አምፊታሚን የተባለውን አደንዛዥ ዕጽ ምርት ውስጥ ይሳተፋል መባሉን መሪው አስተባበሉ።
የሶሪያ መንግሥት የቅርብ ወዳጅ የሆኑት የሄዝቦላህ መሪ ሼክ ሐሰን ናስላላህ በቡድናቸው ላይ የቀረበውን ክስ "ምንም ተአማኒነት የሌለው" ሲሉ አጣጥለውታል።
በቡድኑ ላይ ጥርጣሬ የተፈጠረው ባለፈው ዓመት ሠኔ ወር ላይ 14 ሺህ ኪሎ ግራም የሚመዝን ዕጽ ጣሊያን ውስጥ ከተያዘ በኋላ ነው።
የጣሊያን ባለሥልጣናት እንዳሉት ዕጹ የተጓጓዘው ላታኪያ ከምትባለው የሶሪያ ወደብ ነበረ።
"ዕጹ ከየት እንደመጣ ለማወቅ የጣሊየን ባለሥልጣናትን አግኝተናቸው ነበር" ብለዋል የሄዝቦላህ መሪው ሐሰን ናስራላህ። "ክሱ በተግባር ምንም መሠረት አልነበረውም። በተቃራኒው በአይኤስ፣ በጣሊያንና በሩሲያ የማፍያዎችና በሌሎች የወንጀል ቡድኖች ላይ ምርመራ እያደረጉ ነው" ብለዋል።
መሪው ጨምረውም ሄዝቦላህ "የሐሰተኛ ዜና" ኢላማ ተደርጓል በማለት የምዕራቡ ዓለም "ፕሮፓጋንዳ" ከቀረበባቸው ክስ ጀርባ አለ ብለው እንደሚያምኑ ተናገረዋል።
የአሜሪካና የአውሮፓ ተቋማት የሌባኖሱ ታጣቂ ቡድን ከዕጽ ንግድ ትርፍ እያጋበሰ ነው ሲሉ ለረጅም ጊዜ ሲከሱት ቆይተዋል።
በቴሌቪዥን በተላለፈ ንግግራቸው የሄዝቦላው ዋና ጸሐፊ እንዳሉት "በሁሉም የዕጽ አይነቶች ላይ ያለን አቋም ግልጽ ነው። ማምረት፣ መሸጥ፣ መግዛት፣ ማዘዋወርና መጠቀም በሐይማኖታችን የተከለከለ ነው። አንዳንድ ጊዜ ቅጣቱ እስከ ሞት ሊደርስ ይችላል" ብለዋል።
ጨምረውም ለጠላትም ቢሆን ዕጽን መሸጥ የተከለከለ እንደሆነ ቢጠቅሱም፤ የእስራኤል ፖሊስ ሄዝቦላህ ወደ ግዛቱ ሐሺሽ በድብቅ ያስገባል ሲል ይከሳል።
ሌባኖስ በዓለም ዋነኛ የሐሺሽ አምራች ከሆኑ አገራት መካከል የምትገኝ ሲሆን፤ በኢራን በሚደገፈው በሄዝቦላህ ቁጥጥር ስር የሚገኙ አካባቢዎችን ጨምሮ ዕጹ በግልጽ እንዲበቅል ይደረጋል።

ጣሊያን ውስጥ ከወራት በፊት የታያዘው ዕጽ በጣም ትልቅ የሚባል መጠን ያለው ነበር። በዚህም 85 ሚሊዮን የዕጽ እንክብሎች በማሽን ክፍሎች ውስጥ ተደብቆ በመርከብ ወደጣሊያን ሊገባ ሲል ነበር የተያዘው።
የጣሊያን በገንዘብ ዙሪያ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን የሚከታተለው የፖሊስ ቡድን በቁጥጥር ስር የዋለውና ተቃጥሎ እንዲወገድ የተደረገው ዕጽ 1.2 ቢሊዮን ዶላር ሊያወጣ የሚችል እንደነበር አመልክቶ መጀመሪያ ላይ በአይኤስ ቡድን የተመረተ ነው ብሎ ነበር።
ነገር ግን የዕጹ መጠን በአይኤስ አቅም ሊመረት የሚችል አይደለም በማለት ጥርጣሬውን በሶሪያው ፕሬዝዳንት በሻር አል አሳድ ቁጥጥር ስር ባሉ አካባቢዎች በሚገኙ ፋብሪካዎች ሳይመረት እንዳልቀረ ተጠርጥሯል።
የዕጹን ምንጭ በትክክል ማወቅ ሳይችሉ ከቀሩ በኋላ የጣሊያን ባለሥልጣናት ከዕጹ ጋር በተያያዘ ተጣያቂው ማን እንደሆነ በይፋ ወጥተው አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም።
በአንድ የወንጀለኞች ቡድን ላይ ይደረግ በነበረ ክትትል ምክንያት ዕጹ ሊያዝ እንደቻለ የተነገረ ሲሆን፤ ነገር ግን የቡድኑ ተሳትፎ በአሻሻጭነት ነበር። የዕጹ መድረሻ አውሮፓ ውስጥ ሳይሆን በጦርነት ወደምትታመሰው ሊቢያ እንደሆነ ይታመናል።
የሶሪያ መንግሥትና አጋሮቹ በዕጽ ምርት ትርፍ እያጋበሱ ነው በሚል ክስ ይቀርብባቸዋል። ለዓመታት በዘለቀው ጦርነት ሳቢያ የተከሰተው ሕግ አልባነትና በምዕራባዊያን አገራት በተጣለባት ማዕቀብ ባጋጠማት የገንዘብ እጥረት ሳቢያ ሶሪያ ወደ ሕገ ወጥ የዕጽ ምርት ፊቷን ሳታዞር አልቀረችም ተብሎ ይታመናል።
ከዕጾቹ መካከል ካፕታጎን የሚባለው ዕጽ በግጭት አካባቢ በሚገኙ ተዋጊዎች ዘንድ በስፋት ጥቀም ላይ ይውላል። ካፕታጎን ከመጠን ያለፈ እንቅልፍ የሚያስቸግራቸው ሰዎችን ንቁ እንዲሁኑ የሚያደርግ ነበር። ተዋጊዎቹም በጦርነት ጊዜ ፍርሐታቸውን ለማስወገድ እንደሚጠቀሙበት ተናግረዋል።
ዕጹ የአረቡን ዓለም ያጥለቀለቀ ሲሆን ለመዝናኛነት ይጠቀሙታል። ዕጹ በከፍተኛ መጠን በሳዑዲ አረቢያ፣ በኩዌይትና በዮርዳኖስ ውስጥ ተይዟል። ባለፈው ኅዳር ወር ብቻ ግብጽ ውስጥ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የዕጹ እንክብሎችና በሺዎች ኪሎ የሚገመት ሐሺሽ ከሶሪያ ሲገባ ተይዟል።












