ሕንድ ፡ በአንድ ሆስፒታል ላይ በተከሰተ የእሳት አደጋ 10 አራስ ሕፃናት ሞቱ

ታትሟል

ዛሬ ቅዳሜ ጠዋት በሕንድ አንድ ሆስፒታል ላይ በደረሰ የእሳት አደጋ የሆስፒታሉ ሠራተኞች ህይወት ለማትረፍ የቻሉትን ቢያደርጉም አስር አራስ ሕፃናት ህይወት ማለፉ ተነገረ።

የእሳት አደጋ ተከላካዮች በምዕራባዊው ማሃራሽትራ ግዛት ወደምትገኘው የብሃንዳራ አካባቢ ሆስፒታል እሳቱን ለመቆጠጠር ከመድረሳቸው በፊት ሰባት ሕፃናትን ከእሳት አደጋው ማትረፍ ተችሏል።

የሕንድ ጠቅላይ ሚንስትር ናሬንድራ ሞዲ "ልብ የሚያቆስል አሳዛኝ ክስተት" ሲሉ አደጋውን ገልጸዋል።

የእሳት አደጋው የተከሰተው አርብ ሌሊት ለቅዳሜ አጥቢያ መሆኑን የሆስፒታሉ ኃላፊዎች የገለጹ ሲሆን መንስኤው ምን እንደሆነ እስካሁን ያልታወቀ ነገር የሌለ ሲሆን ምርመራ እየተደረገ ይገኛል።

በእሳቱ ሳቢያ በሆስፒታሉ ውስጥ የተከሰቱት ተከታታይ ፍንዳታዎች የነፍስ አድን ሥራውን ማሰናከሉን የአካባቢው መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

በሥራ ላይ የነበረች አንዲት ነርስ ከሆስፒታሉ አዲስ የተወለዱ አራስ ህጻናት እንክብካቤ ክፍል ውስጥ ጭስ ሲወጣ ካየች በኋላ ለባለስልጣናት ማስታወቋን ተናግራለች።

የአካባቢው የቀዶ ጥገና ሐኪም ፕራሞድ ካንዳቴ እንደገለጹት "የሆስፒታሉ ባለሥልጣናት ሰባት ህፃናትን ቢያድኑም 10 ህጻናት ግን በሚያሳዝን ሁኔታ ሞተዋል" ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ በደረሰባቸው ሐዘን ከሟች ቤተሰቦች ጎን መሆናቸውን በትዊተር ገፃቸው አስታውቀዋል።

የሕንድ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር አሚት ሻህ ስለአደጋው እንዳሉት "ቃላት የማይገልጹት የማይጠገን ጉዳት ነው" ብለዋል።