ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮናቫይረስ ፡ የፋይዘር ክትባት አዲሱ የኮቪድ-19 ዝርያ ላይ 'እንደሚሰራ' ተነገረ
የፋይዘር/ባዮኤንቴክ ክትባት በሁለቱ አዳዲስ የኮሮናቫይረስ ዝርያዎች ላይ ከታየው ለውጥ አንጻርም በሽታውን ለመከላከል እንደሚችል የቤተ ሙከራ ጥናቶች አመለከቱ።
ሆኖም ይህ በአዲሱ የቫይረሱ ዓይነቶች ውስጥ ከሚገኙት ከብዙ ለውጦች ውስጥ አንዱ ይህ ነው።
ጥናቱ ተቀባይነት ቢያገኝም ክትባቱ እንዴት እንደሚሰራ የሚያመለክት የተሟላ ሳይንሳዊ ማስረጃ ተደርጎ እየተወሰደ አይደለም።
በዩናይትድ ኪንግደም እና በደቡብ አፍሪካ አዳዲስ የቫይረሱ ዓይነቶች ተገኝተዋል።
ሁለቱም የቫይረሱ ዓይነቶች በፍጥነት እየተስፋፉ ሲሆን ለእነዚህ ዝርያዎች ምን ዓይነት የመከላከያ ክትባቶች ሊሰጥ ይችላል የሚል ጥያቄ አስነስቷል።
በብዙዎች አመለካከት ክትባቶቹ አሁንም እንደሚሡሩ ቢሆንም ተመራማሪዎች ማረጋገጫ ለማግኘት ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው።
በቴክሳስ ዩኒቨርሲቲ የተደረገው ጥናት በሁለቱም አዲስ ዓይነት ዝርያዎች ውስጥ በሚገኘው ኤን501ዋይ በሚባለው ልውጥ ዝርያ ላይ አተኩሯል።
'መልካም ዜና'
ተመራማሪዎቹ ሁለት የቫይረሱን ዓይነቶች ፈጥረዋል። እነዚህን ቫይረሶች በክሊኒካዊ ሙከራዎች ከተሳተፉ 20 ታካሚዎች በተወሰዱ የደም ናሙናዎች ላይ ምርመራው ተደርጓል።
በውጤቶቹም ክትባት የወሰዱት ሰዎች በሽታ የመከላከል ሥርዓት አዲሱን የቫይረስ ዝርያ ለይቶ ማውጣት መቻላቸውን አሳይቷል።
ከኬምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ራቪ ጉፕታ "የተመረጠው አዲስ ዝርያ በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ከሚገኙ ከስምንቱ አንዱ ብቻ ነው። በእውነቱ ይህ ብቻውን ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራል ተብሎ አይታሰብም ነበር" ብለዋል።
የለንደን የሃይጂን እና ትሮፒካል ሜዲሲን ትምህርት ቤት ባልደረባ የሆኑት ፕሮፌሰር ስቴፈን ኢቫን በበኩላቸው "ተቃራኒው ውጤት ተገኝቶ ቢሆን ኖሮ ... ያ መጥፎ እና በጣም አሳሳቢ በሆነ ነበር" ብለዋል።
"አዎ ይህ ጥሩ ዜና ነው። ነገር ግን የፋይዘር ወይም ሌሎች ክትባቶች በእርግጠኝነት መከላከያ እንደሚሰጡን ገና ሙሉ መተማመን ላይ አልደረስንም" ሲሉ ገልጸዋል።