ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮናቫይረስ ፡ በአንድ ሰው ምክንያት የአውስትራሊያዋ ከተማ የእንቅስቃሴ ገደብ ጣለች
የአውስትራሊያዋ ከተማ ብሪዝበን በአንድ በለይቶ ማቆያነት በማገልገል ላይ ባለ ሆቴል ውስጥ የምትሠራ የጽዳት ሠራተኛ በኮሮናቫይረስ ተይዛ በመገኘቷ ለሦስት ቀናት የሚቆይ የእንቅስቃሴ ገደብ ጣለች።
የጤና ባለሥልጣናት እንዳሉት የጽዳት ሠራተኛዋ ላይ የተገኘው በፍጥነት የሚተላለፈው በዩናይትድ ኪንግደም የተገኘው አይነት ዝርያ ያለው ቫይረስ በመሆኑ ሊስፋፋ ይችላል ብለው ስጋት ገብቷቸዋል።
እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በለይቶ ማቆያ ውስጥ እንዲገቡ ከተደረጉ ተጓዦች ባሻገር ብሪዝበን በጣም ጥቂት ኮሮናቫይረስ ያለባቸው ሰዎች ናቸው የተገኙባት።
በጽዳት ሠራተኛዋ ላይ የተገኘው አዲሱ አይነት የቫይረስ ዝርያ በለይቶ ማቆያ ሆቴል ውስጥ ካሉ ሰዎች ውጪ ባለው የአውስትራሊያ ማኅበረሰብ ውስጥ ሲገኝ ይህ የመጀመሪያው ነው ተብሏል።
ይህ ለቀናት የተጣለው የእንቅስቃሴ ገደብ የኩዊንስላንድ ግዛት ዋና ከተማ በሆነችው ብሪዝበን ውስጥ ባሉ አምስት በርካታ ሕዝብ በሚኖርባቸው አካባቢዎች ነው ተግባራዊ የሚሆነው።
የግዛቲቱ አስተዳዳሪ የሆኑት አንስቴሺያ ፕላሽቻክ ዛሬ አርብ እንቅስቃሴ ገደቡ ስለመጣሉ እንዳስታወቁት፤ እርምጃው የተወሰደው የጽዳት ሠራተኛዋ ተመርምራ ቫይረሱ እንደተገኘባት ከታወቀ ከ16 ሰዓታት በኋላ ነው።
የእንቅስቃሴ ገደቡን መጣል ያስፈለገው የቫይረሱን መስፋፋት በተቻለ ፍጥነት ለመቆጣጠር በማሰብ እንደሆነ ባለሥልጣኗ ገልጸው "ለሦስት ቀናት የእንቅስቃሴ ገደብ መጣል ከዘገየን በኋላ ወደፊት ሊጣል የሚችለውን የ30 ቀናት ገደብን ለማስቀረት ይረዳል" ብለዋል አስተዳዳሪዋ።
"በዩናይትድ ኪንግደምና በዓለም ዙሪያ ባሉ በሌሎች ቦታዎች ላይ በዚህ አዲስ አይነት የቫይረስ ዝርያ ምክንያት እየተከሰተ ያለውን የበሽታው በፍጥነት መስፋፋትን ሁሉም በኩዊንስላንድ ግዛት ውስጥ ያሉ ሰዎች ያውቁታል ብለን እናስባልን" በማለት የእርምጃውን ምክንያት ገልጸዋል።
ጨምረውም እንዲህ አይነቱ በፍጥነት የሚዛመት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ "እዚህ በታላቁ ግዛታችን ውስጥ እንዲከሰት አንፈልግም" ብለዋል።
ወረርሽኙ ከተከሰተ በኋላ አስካሁን ድረስ አውስትራሊያ 28,500 በኮሮናቫይረስ መያዛቸው የተረጋገጠ ሰዎችን ያገኘች ሲሆን፤ በበሽታው ሰበብም 909 ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል።
ከዓለም አገራት ውስጥ በበሽታው ክፉኛ የተመታችው አሜሪካ ስትሆን አስካሁን ከ21 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የወረርሽኙ ቫይረስ በምርመራ የተገኘባቸው ሲሆን 362 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ሰበብ ሕይወታቸውን አጥተዋል።