ኮሮናቫይረስ፡ በኮቪድ-19 ምክንያት የሚከሰት ሞትን ይቀንሳሉ የተባሉ ሁለት መድኃኒቶች ተገኙ

ታትሟል

ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ በኮሮናቫይረስ ምክንያት የሚከሰት ሞትን በአንድ አራተኛ ይቀንሳሉ የተባሉ ሁለት መድኃኒቶች ተገኙ።

እነዚህ መድኃኒቶች የሚሰጡት በጠብታ ሲሆን ሙከራው በተደረገባቸው ሕሙማን ላይ ከፍተኛ ለውጥ አምጥተዋል ተብሏል።

ባለሙያዎቹ አክለውም በዩናይትድ ኪንግደም የመድኃኒቱ አቅርቦት በበቂ ሁኔታ ስላለ በፍጥነት ጥቅም ላይ ሊውሉ ይችላሉ ሲሉ ተናግረዋል።

እነዚህ ቶሲሊዙማብ (tocilizumab) እና ሳሪሉማብ (sarilumab) የተሰኙ መድኃኒቶች በዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ውስጥ በስፋት እንደሚገኙ ተገልጾ፣ የኮሮናቫይረስ ሕሙማንን ሕይወት ከመታደግ ባለፈ፣ በፍጥነት እንዲያገግሙ በማድረግ እንዲሁም በጽኑ ሕሙማን ክፍል የሚኖራቸውን ቆይታ በማሳጠር ረገድ አስተዋጽኦ አላቸው ተብሏል።

በዩናይትድ ኪንግደም ሆስፒታሎች ውስጥ 30,000 በኮሮናቫይረስ ምክንያት የታመሙ የሚገኙ ሲሆን ይህም ባለፈው ዓመት ሚያዚያ ከነበረው ጋር ሲነጻጸር በ39 በመቶ ይልጣል።

የዩኬ መንግሥት ከመድሃኒቶቹ አምራቾች ጋር የመድኃኒቶቹ አቅርቦት በበቂ ሁኔታ እንዲገኝ እየሰራ እነደሆነ ገልጿል።

ሁለቱም መድኃኒቶች በእኩል የሚያገለግሉ ሲሆን ከዚህ ቀደም ዴክሳሜትሶን (dexamethasone) በተሰኘው መድኃኒት ላይ የተገኘው ጥቅም ላይ ግብዓት በመሆን ያገለግላሉ ተብሏል።

መድኃኒቶቹ ዋጋቸው ከፍ ያለ ሲሆን በታካሚ ከ700 ፓውንድ እስከ 1000 ፓውንድ እንደሚያስወጡ ተገልጿል።

ምርምሩን በቀዳሚነት የመሩት የኢምፔሪያል ኮሌጁ ፕሮፌሰር አንቶኒ ጎርደን "ይህንን መድኃኒት የሰጠናቸው እያንዳንዳቸው 12 ሕሙማን ሕይወታቸው ከሞት ታድጎት ተመልክተናል። ትልቅ ለውጥ ነው" ብለዋል።

የእንግሊዝ ብሔራዊ ጤና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ስቴፈን ፖዊስ በበኩላቸው "በአሁኑ ጊዜ በኮቪድ-19 የታመሙ ሰዎችን ሞት የሚቀንስ መድኃኒት መምጣቱ ትልቅ ዜና ነው፤ እንዲሁም ከቫይረሱ ጋር ለምናደርገው ፍልሚያ ትልቅ እድገት ነው" ብለዋል።

የጤና እና ማኅበራዊ ክብካቤ ሚኒስትር ማት ሀንኮክ "ዩኬ አሁንም ለኮሮናቫይረስ ሕሙማን የሚሆኑ መድኃኒቶችን በመለየትና በማግኘት ቀዳሚ መሆኗን አሳይታለች" ብለዋል።

የኮሮናቫይረስን የሚያክሙ የጤና ባለሙያዎች ከዴክሳሜትሶን ጎን ለጎን ሁለቱን መድኃኒቶች እንዲሰጡ ታዟል።

እነዚህም መድኃኒቶችንም ከዩናይትድ ኪንግደም ወደ ሌላ አገራት መላክ ላይም እገዳ ተጥሏል።

ይህ የምርምር ውጤት በሕክምና ጆርናሎች ላይ ያልታተመ ሲሆን አንዲሁም በአቻ ባለሙያዎችም ግምገማ አልተደረገበትም።