ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮናቫይረስ ፡ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ የተገኘው አዲሱ የኮቪድ-19 ዝርያ ክትባት መቋቋሙን የሚያመለክት ነገር የለም
ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ተገኘ የተባለው አዲስ አይነት የኮሮናቫይረስ ዝርያ ለሰዎች እየተሰጠ ያለውን ክትባት እንደሚቋቋም የሚያሳይ ምንም ምልክት እንደሌለ የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ።
የዓለም ጤና ድርጅት የቴክኒክ ኃላፊ ዶክተር ማሪያ ቫን ኬርሆቬ እንዳሉት በተለያየ አይነት የኮሮረናቫይረስ ዝርያዎች የተያዙ ሰዎች ተመሳሳይ የሆነ የበሽታውን ምልክት የሚያሳዩ ሲሆን አስካሁን የከፋ ምልክት አልታየም ብለዋል።
ነገር ግን አዲሱ የቫይረስ ዝርያ የበሽታውን የመስፋፋት ፍጥነት ከፍ ማድረጉን ዶክተሯ ተናግረዋል።
"አዲሱን አይነት ቫይረስ በክትባቱ ላይ ያሰደረው ተጽእኖን የሚያመለክት ነገር የለም። ይህ መልካም ዜና ነው። እስካሁን ያለን መረጃ ይህ ነው፤ ጥናቶች ግን እየተካሄዱ ነው" ብለዋል ዶክተር ቫን ኬርሆቬ።
የዓለም ጤና ድርጅት ከፍተኛ ባለስልጣን የሆኑት ማይክ ርያን እንዳሉት አዲሱ የቫይረስ ዝርያ ወረርሽኙ በሚተላለፍበት መንገድ ላይ ምንም ለውጥ አላመጣም።
በአፍሪካ አዲሱ አይነት የኮሮናቫይረስ ዝርያ እንደተገኘባት በተገለጸችው ደቡብ አፍሪካ ወረርሽኙ በከፍተኛ ፍጥነት እየተስፋፋ በርካታ ሰዎችን ለሞት እየዳረገ መሆኑ ተነግሯል።
አዲሱን የቫይረስ ዝርያ ለመቆጣጠር እየጣረች በምትገኘው ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ትናንት ረቡዕ በወረርሽኙ የተነሳ እስካሁን በአንድ ቀን ከተመዘገበው የሚበልጥ የሞት እና አዲስ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር ተመዝግቧል።
የአገሪቱ ጤና ሚኒስትር ዝዌሊ ምኼዜ እንዳሳወቁት 21,832 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ሲታወቅ 844 ሰዎች ደግሞ ህይወታቸውን አጥተዋል። ከሞቱት ውስጥ አብዛኞቹ ምሥራቃዊ ኬፕ በምትባለው ግዛት ውስጥ የሚኖሩ ናቸው።
ከዚህ በፊት በአንድ ቀን ከፍተኛ ሞት ተብሎ የተመዘገበው በሐምሌ ወር ሲሆን በዚህም 572 ሰዎች መሞታቸው ተነግሮ ነበር።
በደቡብ አፍሪካ እስካሁን በኮሮናቫይረስ ምክንያት 31,368 መሞታቸው የተመዘገበ ሲሆን፤ በአጠቃላይ ቫይረሱ እንደተገኘባቸው የተረጋገጡ ሰዎች ቁጥር ደግሞ ከ1.1 ሚሊዮን በላይ ነው።
በአገሪቱ እንዳለ የተደረሰበትና በፍጥነት የሚተላለፈው አዲሱ አይነት የኮረናቫይረስ ዝርያ በበሽታው ለተያዙ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ፍጥነት መጨመር ምክንያት ሊሆን ይችላል ተብሎ ይታመናል።