የካናዳ ዜግነት ተሰጥቷቸው የነበሩ አሜሪካውያን እንዲመልሱ ተነገራቸው

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በቅርቡ የካናዳ ዜግነት ያገኙ አሜሪካውያን ለተጨማሪ ምርመራ ስለሚፈለግ በሚል የዜግነት ምስክር ወረቀታቸውን እንዲመልሱ መጠየቃቸው ግርታ እና ቅሬታ እንደፈጠረባቸው ተናገሩ።

በካናዳ የኢምግሬሽን ሚኒስቴር የተላከ እና ቢቢሲ የተመለከተው ደብዳቤ ዜግነቱ "በስህተት ተሰጥቷቸው ሊሆን ስለሚችል" እንዲመልሱ ይጠይቃል።

ደብዳቤው ለምን ያህል ሰዎች እንደተላከ የማይታወቅ ሲሆን ዜግነቱ የተሰጣቸው በታህሳስ ወር ከካናዳ ጋር የዘር ግንዳቸው የሚተሳሰር ሰዎችን በሚመለከት በወጣ አዲስ ሕግ መሠረት ነው።

የኢምግሬሽን ሚኒስቴር ለቢቢሲ በሰጠው ምላሽ "ውስን ሰነዶች ላይ" ምርመራ እየተደረገ መሆኑን አስታውቋል።

ምርመራው "በተናጠል ጉዳዮች ላይ ባለን ጥርጣሬ" የተነሳ መሆኑን ቃል አቀባዩ ተናግረው የምስክር ወረቀታቸውን እንዲመልሱ የተነገራቸው ግለሰቦች ተጨማሪ ማስረጃ እንዲያቀርቡ እንደሚደረግ ተናግረዋል።

"ምርመራው ግለሰቦቹ ዜግነቱ እንደሚገባቸው የሚያሳይ ከሆነ ይመለስላቸዋል" ሲሉ ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።

ከካሊፎርኒያ ወደ ብሪቲሽ ኮሎምቢያ በቅርቡ የሄደው ሾን ዳቪስ ሙኒ ደብዳቤው ሲደርሰው መደንገጡን ይናገራል።

"ከምገምተው በላይ ነው ያስደነገጠኝ" ብሏል።

ሙኒ የካናዳ ዜግነት ያመለከተው "የጠፉ ካናዳውያን" የሚለው አዲሱ ሕግ በዚህ ዓመት ተግባራዊ መሆን ከጀመረ በኋላ ነው።

ከጠበቃው ጋር በመሆን ቅድመ አያቶቹ በካናዳ ኒው በረንስዊክ መወለዳቸውን የሚያሳይ 114 ገጽ ሰነድ ማስገባቱን ይናገራል።

በካናዳ የዜግነት ቢሮ ኃላፊዎች የተፈረመው ደብዳቤ ምስክር ወረቀቱን እንዲመልስ የተደረገው ተገቢውን ሰነድ ማቅረብ ስላለስቻለ መሆኑን ይገልጻል።

ሙኒ ደብዳቤው እርሱን እና ጠበቃውን ግራማጋባቱን ጠቅሶ ማመልከቻው የተሟላ መሆኑን ይከራከራል።

"ከሁሉ የከፋው አጭበርባሪዎች አስመስሎ ነው ያቀረበን። ወይንም ደግሞ የሆነ ስህተት የሠራን" ብሏል።

ካናዳ "የጠፉ ካናዳውያን" የሚለውን ሕጓን ባወጣች በአንድ ወር ከግማሽ ውስጥ 12 ሺህ ማመልከቻዎችን ተቀብላለች።

አብዛኛዎቹ ዜግነቶች የተሰጡት በአሜሪካ ለተወለዱ መሆኑን የመንግሥትን መረጃ ጠቅሶ ሲቢሲ ዘግቧል።

ቀጥሎ ዜግነት ይሰጣቸዋል ተብሎ የሚጠበቁት ሜክሲኮ እና ዩናይትድ ኪንግደም የተወለዱ ናቸው።

ማመልከቻቸው ውድቅ የተደረገባቸው ሰዎች መረጃ ለሕዝብ ይፋ አልሆነም።

የካናዳ ኢሚግሬሽን ሚኒስቴር እያንዳንዱ ማመልከቻ የዜግነት ምስክር ወረቀቱ ከመሰጠቱ በፊት "ስልጠና በወሰኑ ኦፊሰሮች" ይመረመራል ብሏል።

ይሁን እንጂ እነዚህ ምርመራ እየተደረገባቸው ያሉ ማመልከቻዎች "በሚገባ ወጥ በሆነ መልኩ እና ከሕጉ አንጻር ጉዳያቸው መታየቱን" ለማረጋገጥ መሆኑ ተገልጿል።