አዲሱ የኮቪድ-19 ክትባት የሰውነት መቆጣት ሊያስከትል ይችላል ተባለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከፍተኛ የሆነ አለርጂ (የሰውነት መቆጣት) የሚያጋጥማቸው ሰዎች አዲሱን የፋይዘር/ባዮንቴክ ክትባት መውሰድ አይኖርባቸውም ሲሉ የዩኬ መድሃኒት ተቆጣጣሪዎች አስታወቁ።
ይህ የተባለው ሁለት የዩኬ ጤና ባለሙያዎች ክትባቱን ከወሰዱ በኋላ የሰውነት መቆጣት ስላጋጠማቸው ነው።
የመድሃኒት ተቆጣጣሪ ኤጀንሲው ከዚህ ቀደም የምግብ፣ የመድሃኒት እና የክትባት አለርጂ (የሰውነት መቆጣት) ያለባቸው ሰዎች የፋይዘር/ባዮንቴክ ክትባትን መውሰድ የለባቸውም ብሏል።
ሁለቱ አለርጂ ያጋጠማቸው የጤና ባለሙያዎች አለርጂው ያጋጠማቸው ክትባቱን እንደወሰዱ መሆኑ ተነግሯል። ሁለቱ የጤና ባለሙያዎች ሕክምና ተደርጎላቸው አስጊ ሁኔታ ውስጥ አይደሉም ተብሏል።
ሁለቱ የጤና ባለሙያዎች ሰውነታቸው ላይ ሽፍታ እንደወጣ፣ የደም ግፊታቸው ቀንሶ እንደነበረ እና የመተንፈስ ችግር አጋጥሟቸው እንደነበረም ተጠቅሷል።
ሁለቱም የብሔራዊ ጤና አገልግሎት ሠራተኞች ከፍተኛ የሆነ የሰውነት መቆጣት (አለርጂ) ያለባቸው ናቸው።
ዩናይትድ ኪንግደም ከትናንት ጀምሮ ለዜጎቿ የኮሮናቫይረስ ክትባት መስጠት መጀመሯ ይታወሳል።
አሁን መሰጠት የተጀመረው የኮቪድ-19 ክትባት በዋናነት ትኩረት ያደረገው ለበሽታው በከፍተኛ ደረጃ ተጋላጭ የሆኑትን ሰዎች ሲሆን በቀጣይም ለሌሎች እንደሚዳረስ ተነግሯል።
የአሜሪካ እና የጀርመን ኩባንያ የሆኑት ፋይዘር እና ባዮንቴክ ያበለጸጉት ክትባት ዩናይትድ ኪንግደም ለዜጎቿ እንዲሰጥ የመድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን መፍቀዱ ይታወሳል።
ዩኬ ይህን ክትባት በመጠቀም የመጀመሪያዋ አገር ሆናለች።
95 በመቶ ቫይረሱን የመከላከል አቅምን ያጎለብታል የተባለለትን ክትባት፤ ሰዎች በ21 ቀናት ልዩነት ሁለት ጊዜ መወጋት ይኖርባቸዋል። ሰዎች ከቫይረሱ ራሳቸውን መከላከያ የሚጀምሩት ሁለተኛውን ክትባት ከወሰዱ ከሰባተኛው ቀን በኋላ ነው ተብሏል።












