የኬንያና የሶማሊያ እሰጥ አገባ የጫት ንግድን እየጎዳው ነው ተባለ

ታትሟል

ኬንያ እና ሶማሊያ የገቡበት ዲፕሊማሲያዊ እስጥ አገባ በጫት ንግድ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ማሳደሩ ተነገረ።

የሶማሊያ መንግሥት ከኬንያ በሚገባ የጫት ምርት ላይ እግድ መጣሉን ተከትሎ ጫት አምራች ኬንያውያን ገበሬዎች ከፍተኛ ኪሰራ እየገጠማቸው መሆኑ ተግልጿል።

ሶማሊያ ከወራት በፊት ከኬንያ በሚገባው የጫት ምርት ላይ እግድ የጣለችው የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ምክንያት በማድረግ ነበር። ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን የኬንያ የጫት ምርት ወደ ሶማሊያ ከመግባቱ በፊት ኬንያ ቅድመ ሁኔታዎችን ማሟላት ይኖርባታል ትላለች ሶማሊያ።

ሶማሊያ የኬንያን የጫት ምርት ወደ አገሬ ከማስገባቴ በፊት ኬንያ በውስጣዊ ጉዳዬ ጣልቃ ከመግባት መቆጠብ ይኖርባታል፣ የሶማሊያን አየር ክልል ማክበር ይኖርባታል፤ እንዲሁም እንደ ስኳር፣ ወተት እና ማር ያሉ የሶማሊያ ምርቶችን እንድትቀበል ጠይቃለች።

ኬንያ በበኩሏ በሶማሊያ ውስጣዊ ጉዳይ ጣልቃ አለመግባቷን እና ፍትሃዊ ከሆነ የንግድ ስምምነት ለመድረስ ዝግጁ መሆኑኗን ትገልጻለች።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን ሶማሊያ ከኢትዮጵያ የጫት ምርት ማስገባቷን ቀጥላለች። ሶማሊያ በአብዛኛው የጫት ምርትን የምታገኘው ከኢትዮጵያና ከኬንያ ነው።

በምስሥቃዊ ኬንያ የምትገኘው ሜሩ ጫት በማብቀል ትታወቃለች። ወደ ሶማሊያ ይላክ የነበረው የጫት ምርት ላይ እግድ መጣሉን ተከትሎ ጫት አምራች ገበሬዎች ለችግር ተጋልጠናል እያሉ ነው።

የዘጠኝ ልጆች እናት የሆነችው ሜሪ ናቶንጃ “አረንጓዴው ወርቅ” የምትለውን ጫት ለበርካታ ዓመታት ስታመርት ቆይታለች። የጫት ምርት ወደ ዩናይትድ ኪንግደም እና ሶማሊያ በሚላክበት ወቅት ጥሩ ገቢ ታገኝ እንደነበረም ሜሪ ታስታውሳለች።

ከስድስት ዓመታት በፊት ዩናይትድ ኪንግደም ጫት ወደ አገሬ አይገባም ስትል ወሰነች። ባሳለፍነው ዓመት ሕዳር ወር ላይም ሶማሊያ ከኬንያ በሚገባ የጫት ምርት ላይ ገደብ ጣለች። ይህን ጊዜ ሜሪ እሷ እና መሰል በሺዎች የሚቆጠሩ ጫት አምራች ገበሬዎች ሕይወታቸው መፈተኑን ትናገራለች።

“ሕይወት ፈተና ሆኖብናል። ገንዘብ በእጃችን የለም። መልበስ እና መብላት ከባድ ሆኖብናል። ልጆቻችን ጾማቸውን እያደሩ ነው። በየሦስት ወሩ ምርት እየሰበሰብን ከአንድ እስከ አምስት ሺህ ዶላር እናገኝ ነበር። አሁን ግን አንድ ዶላር እንኳን ማግኘት አንችልም።”

የኬንያ የጫት ነጋዴዎች ማኅበር እንደሚለው ከሆነ የኬንያ ጫት አምራች ገበሬዎች ከዚህ ቀደም እስከ 50 ቶን የሚመዝን ጫት ወደ ሶማሊያ በመላክ እስከ 140 ሺህ ዶላር ድረስ ገቢ ያስገኙ ነበር።

አሁን ላይ ገበሬዎች ከምርታቸው እጅግ አነስተኛ የሚሆነውን ለኬንያ ገበያ ካቀረቡ በኋላ ሌላው ፈላጊ ስለሌለው ምርቱ እየተጣለ ነው ይላል ማኅበሩ።

ባሳለፍነው ወር በሶማሊያ እና በኬንያ መካከል ያለው ዲፕሎማሲያዊ አለመግባባት ተካሮ ሶማሊያ የኬንያን አምባሳደር አባራ በናይሮቢ የሚገኘውን አምባሳደሯን መጥራቷ ይታወሳል።