ኮሮናቫይረስ ፡ አርጀንቲና በኮቪድ-19 ሰበብ ባለሀብቶች ላይ አዲስ ግብር ጣለች

አገሪቱ ምክር ቤት በአዲሱ ግብር ላይ ሲወያይ ሰልፈኞች በምክር ቤቱ ዙሪያ ተሰብስበው ነበር

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, አገሪቱ ምክር ቤት በአዲሱ ግብር ላይ ሲወያይ ሰልፈኞች በምክር ቤቱ ዙሪያ ተሰብስበው ነበር
ታትሟል

አርጀንቲና ለኮሮናቫይረስ ታማሚዎች ሕክምና የሚያስፈልጉ የሕክምና አቅርቦቶችን ለማሟላትና ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችላትን ወጪ ለመሸፈን ሀብታም ዜጓቿ ላይ አዲስ ግብር ጣለች።

ይህ አንድ ጊዜ የሚከፈለውና "የሚሊየነሮች ግብር" የተባለውን ታክስ ለመጣል የወጣው ረቂቅ ለአርጀንቲና ምክር ቤት አባላት ቀርቦ 26 እንደራሴዎች ቢቃወሙትም የ42ቱን ድጋፍ በማግኘቱ ጸድቋል።

ይህ ግብር ይመለከታቸዋል የተባሉት የአርጀንቲና ባለጸጋዎች ሀብታቸው ከ25 ሚሊዮን ዶላር በላይ ሲሆን ብዛታቸውም 12 ሺህ እንደሚሆኑ ታውቋል።

አርጀንቲና እስካሁን 1.5 ሚሊዮን ዜጎቿ በኮሮናቫይረስ መያዛቸውን ያረጋገጠች ሲሆን 40 ሺህ የሚደርሱት ደግሞ በበሽታው ሳቢያ ለሞት ተዳርገውባታል።

አርጀንቲና በወረርሽኙ ክፉኛ ከተመቱ የዓለም አገራት መካከል አንዷ ስትሆን ባለፈው ጥቅምት ወር ላይ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ህሙማን በማስመዝገብ አምስተኛዋ አገር ሆናለች።

አገሪቱ ያላት አጠቃላይ ሕዝብ 45 ሚሊዮን የሚደርስ ሲሆን ከቁጥር አንጻር በበሽታው የተያዙ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከተገኙባቸው አገራት መካከል ትንሽ የሕዝብ ቁጥር ያላት አገር ሆናለች።

ከሁለት ዓመት በፊት ጀምሮ የምጣኔ ሀብት ቀውስ ውስጥ የምትገኘው አርጀንቲና የበሽታውን መስፋፋት ለመግታት በሚል የተጣለው የእንቅስቃሴ ገደብ በሥራ አጥነት፣ በድህነትና በመንግሥት ዕዳ ላይ ተጨማሪ ጫናን ፈጥሯል።.

በአገሪቱ ባለሀብቶች ላይ የተጣለው አዲሱ ግብር ከአጠቃላዩ ግብር ከፋይ 0.8 በመቶውን ብቻ የሚመለከት መሆኑን የግብሩን ደንብ ካረቀቁት ሰዎች መካከል አንዱ ተናግረዋል።

ግብሩን ይከፍላሉ ተብለው የሚጠበቁት ሚሊየነሮች በአገር ውስጥ ካላቸው ሀብት እየጨመረ በሚሄድ ሁኔታ አስከ 3.5 በመቶ እንዲሁም በውጪ አገር ካላቸው ሀብት ደግሞ 5.25 በመቶ እንደሚሆን ተገልጿል።

የፈረንሳይ ዜና ወኪል ኤኤፍፒ እንደዘገበው፤ በአዲሱ ግብር አማካይነት ከሚሰበሰበው ገንዘብ ውስጥ 20 በመቶው ለሕክምና አቅርቦቶች፣ 20 በመቶው ለአነስተኛና መካከለኛ የንግድ ተቋማት ድጋፍ፣ 20 በመቶው ለተማሪዎች የነጻ ትምርት ዕድል ድጋፍ፣ 15 በመቶው ለማኅበራዊ ልማትና ቀሪው 25 በመቶው ደግሞ ለተፈጥሮ ጋዝ ፍለጋ ሥራ ይውላል።

በአዲሱ ታክስ አማካይነት በፕሬዝዳንት አልቤርቶ ፈርናንዴዝ የሚመራው የአርጀንቲና መንግሥት 300 የአርጀንቲና ፔሶ ወይም ከ3 ቢሊዮን ዶላር በላይ ያገኛል ተብሎ ይጠበቃል።

ነገር ግን ተቃዋሚዎች አዲሱ ግብር እንደተባለው የአንድ ጊዜ ብቻ ላይሆን እንደሚችልና የውጭ መዋዕለ ነዋይ አፍሳሾችን ሊያሸሽ ይችላል በማለት ስጋታቸውን ገልጸዋል።

አንደኛው ተቃዋሚ ፓርቲ አዲሱን ሕግ ሀብት "የመውረስ" ድርጊት ሲል ተቃውሞታል።