ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአስከሬን ማቆያ ክፍል 'ከሞት ተነሳ' የተባለው ኬንያዊ ሞተ
ባለፈው ሳምንት ሞቷል ተብሎ አስከሬን ማቆያ ክፍል ገብቶ የነበረው ኬንያዊ 'ከሞት ተነስቷል' መባሉ አገር ጉድ ቢያሰኝም እንደገና መሞቱ ተነግሯል።
ግለሰቡ ሞቷል በሚል በአንድ ሆስፒታል ውስጥ የአስከሬን ማቆያ ክፍል ሠራተኛ አስከሬኑን ለመገነዝ ሲያዘጋጁ በነበረበት ወቅት ነው "ሟቹ" ድንገት ጮሆ የተነሳው ከዚያም ተዝለፍልፎ ወደቀ።
የ32 ዓመቱ ፒተር ኪገን በማይድን በሽታ ለረዥም ጊዜ ሲሰቃይ የነበረ ሲሆን ከሰሞኑም ሆስፒታል ህክምና ካደረገ በኋላ ወደቤቱ መመመለሱ ተነግሯል።
ከሞት ከተረፈ በኋላም ከኬንያው ደይሊ ኔሽን ጋዜጣ ጋር ባደረገው ቆይታ በህይወት በመቆየቱ ደስተኛ መሆኑን ተናግሮ ነበር።
"ይህ የአምላክ ሥራ ነው" ማለቱንም ጋዜጣው አስነብቧል።
አክሎም ''ድንገት ስነቃ የት እንዳለሁ እንኳን አላውቅም ነበር። ነገር ግን ፈጣሪ ሕይወቴን ስላተረፈልኝ በጣም ደስተኛ ነኝ። ከዚህ በኋላ ሕይወቴን ሙሉ እሱን በማገልገል ነው የማሳልፈው'' ብሎ ነበር።
ታሪኩ በርካቶችን ያሰደመመ ሲሆን በማኅበራዊ ሚዲያዎችም መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።
ከዚህም በተጨማሪ ግለሰቡ በሚኖርባት ኬሪቾ ግዛት የሕዝብ ተመራጮች ዘንድ በተደረገ ጉባኤ መከራከሪያም ሆኖ ነበር።
ተመራጮቹ ይህንን የሚመረምር ቡድን እንዲቋቋምም አዘዋል። ሆኖም የወጣው ሪፖርት እንደሚያመለክተው የጤና ባለሙያዎችን ነፃ አድርጓቸዋል።
ግለሰቡ በትናንትናው ዕለት እንዳረፈ የቤተሰቡ ቃለ አቀባይ ለስታንዳርድ ጋዜጣ ተናግረዋል።
"ኪገን ኬሪቾ ሆስፒታል እንደደረሰ መሞቱን የጤና ባለሙያዎች አረጋግጠዋል። መጀመሪያ ሲታከም የነበረው ካፕካቴት የተባለ የጤና ማዕከል ውስጥ ሲሆን ለበለጠ ህክምና ነው ወደ ኬሪቾ የተዛወረው" በማለት ቃለ አቀባዩ ሄዝቦን ቶኑይ ተናግረዋል።