የጓቲማላ ተቃዋሚዎች ምክር ቤቱን በእሳት አቃጠሉ

የጓቲማላ ምክር ቤት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

በመቶዎች የሚቆጠሩ ጓቲማላውያን ተቃዋሚዎች የአገሪቱን ምክር ቤት ህንፃ መዝብረው እሳት ለቀውበታል ተብሏል።

ፖሊስም ተቃዋሚዎችን ለመበተን አስለቃሽ ጋዝ ተጠቅሟል። የተወሰነው የህንፃው ክፍልም በቃጠሎው ጉዳት ደርሶበታል።

የእሳት አደጋ አገልግሎት ሰራተኞች እሳቱን ማጥፋት ቢችሉም በርካታ ሰዎችም በጭሱ ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ ህክምናም እየተደረገላቸውይገኛሉ።

ከሰሞኑ ምክር ቤቱ ያፀደቀውን በጀት በመቃወምም ነው ተቃውሟቸውን እየገለፁ ያሉት።

በጀቱ ትልልቅ የልማት ፕሮጀክቶች ከመንግሥት ጋር ግንኙነት ያላቸው ኩባንያዎች እንዲሰሯቸው በማድረግ ቅድሚያ ሰጥቷል። በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ከፍተኛ የማህበራዊና ምጣኔ ኃብታዊ ጫና የደረሰባቸውን የማህበረሰቡ አካላትን ችላ ብሏልም በማለት እየወቀሱ ይገኛሉ።

ከዚህም በተጨማሪ በትምህርትና በጤና ላይ ከፍተኛ የሆነ የበጀት ቅነሳ መደረጉም ተቃዋሚዎችን ያበሳጨ ጉዳይ ሆኗል።

ሌላው ተቃዋሚዎቹ ዋነኛ ቁልፍ ጉዳይ ብለው የሚያነሱት ጓቲማላ በኤታና ኢዮታ በተባሉት አውሎ ንፋስ መመታቷን ተከትሎ ህዝቧ እንዲህ አይነት ውርጅብኝ ባለበት ወቅት ፓርላማው ሆን ብሎ የወሰነው ውሳኔ ነው ይላሉ።

ፓርላማው ህዝቡ በተደናገረበት ወቅት ይህንን ውሳኔ መወሰኑም አስተችቶታል።

የአገሪቱ ፕሬዚዳንት አሌሃንድሮ ጊማቴይ ከስልጣናቸው እንዲለቁ ተቃዋሚዎች በመጠየቅ ላይ ናቸው።

በትናንትናውም እለት ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ የተሳተፈበት የተቃውሞ ሰልፍ የተደረገ ሲሆን በአንፃራዊነትም ሰላማዊ ነው ተብሏል።

ምክትል ፕሬዚዳንቱ ጉይሌርሞ ካስቲሎ በበኩላቸው በጀቱ ላይ ያላቸውን ተቃውሞ የገለፁ ሲሆን እሳቸውም ሆነ ፕሬዚዳንቱ "ለአገሪቱ ደህንነት ሲባል ከስልጣን መውረድ አለብን" ብለዋል።