ባለቤቱን ገድሎ ያቃጠለው ፈረንሳያዊ በ25 አመት እስር ተቀጣ

የፎቶው ባለመብት, AFP
ባለቤቱን ገድሎ በማቃጠል መላ ፈረንሳይን ያስደነገጠው ግለሰብ በ25 አመት እስራት ተቀጥቷል።
አሌክሳ ዳቫል የተሰኘችው ባለቤቱ አስከሬኗ ተቃጥሎ የተገኘው ግሬይ በምትባል ከተማ ከሶሰት አመት በፊት ነበር።
ባላቤቷ ጆናታን ዴቪል ሚስቱ የአካል እንቅስቃሴ ለማድረግ ለሩጫ ብላ ወጥታ አልተመለሰችም በማለት ለፖሊስ ሪፖርት አድርጎ ነበር።
በኋላ ግን ደብድቦ እንደገደላትና ሬሳዋንም እንዳቃጠለው ተናዟል።
የ36 አመቱ ግለሰብ በትናንትናው እለት ሲሆን የተፈረደበት ከዚህ ቀደም ለባለቤቱ ቤተሰቦች "አዝናለሁ" ከማለት ውጭ ሌላ ምንም ያለው ነገር የለም ተብሏል።
አቃቤ ህግ በበኩሉ ግለሰቡ ላጠፋው ጥፋት የእድሜ ልክ እስራት ይገባዋልም በሚል ተከራክሯል።
የ29 አመቷ አሌክሲያ ዳቫል የባንክ ሰራተኛ ነበረች። ከሶስት አመት በፊት ነበር ባለቤቷ ለሩጫ እንደወጣች አልተመለሰችም በማለት ሪፖርት ለፖሊስ ያደረገው።
ከሁለት ቀናት በኋላ ከምትሮጥበት አካባቢ ራቅ ብሎም አስከሬኗ ተቃጥሎና በዛፍ ቅርንጫፎች ተሸፍኖ ተገኝቷል።
አሟሟቷ በርካቶችን አስደንግጧል፤ ልብም ነክቷል። በስሟም ትኖርባት በነበረው ከተማ ግሬይ 10 ሺህ ሰዎች የተሳተፉበትም ሩጫ ተካሂዷል።
ከዚህም በተጨማሪ በርካታ ሴቶችም በመላ ፈረንሳይ በመሮጥ ስሟን ዘክረውታል።
መሞቷ ከታወቀ በኋላም ባለቤቷ ከአማቾቹ ጋር በመሆን ጋዜጣዊ መግለጫዎች ላይ እንባ እየተናነቀው ታይቷል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሆኖም ከሶስት ወራት በኋላ ሚስቱን መግደሉን መናዘዙን አቃቤ ህግ አስታውቋል። መጀመሪያ ላይ አስከሬኗን አላቃጠልኩም ብሎ ቢክድም በኋላ ላይ አምኗል።
ለበርካታ ጊዜያትም በፍርድ ሂደቱ ወቅት ቃሉን መቀያየሩ ተገልጿል።
በዚህ ሳምንት ዳኛው "በግድያው ብቸኛው ተጠያቂ አንተ ነህ ወይ? "ብለው በጠየቁበት ወቅት "አዎ" የሚል ምላሽ ሰጥቷል።












