ኮሮናቫይረስ፡ የፕሬዝዳንት ትራምፕ ልጅ ኮቪድ-19 ተገኘበት

የትራምፕ ልጅ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

የዶናልድ ትራምፕ ልጅ ዶናልድ ትራምፕ ጁንየር ኮሮናቫይተስ እንደተገኘበት ቃል አቀባዩ ተናገረ።

የ42 ዓመቱ ትራምፕ ጁንየር በሳምንቱ መባቻ ላይ ነው በቫይረሱ መያዙ የታወቀው። አሁን ራሱን ለይቶ ይገኛል።

እስካሁን የበሽታውን ምልክቶች እንዳላሳየና በህክምና ባለሙያዎች የሚሰጠውን መርህ እየተከተለ መሆኑ ተገልጿል።

ሌላው የትራምፕ ልጅ የ14 ዓመቱ ባሮን ትራምፕ ባለፈው ወር በወረርሽኙ ተይዞ በፍጥነት ማገገሙ ይታወሳል።

ትራምፕ ጁንየር በአባቱ የምርጫ ቅስቀሳ ጉልህ ሚና ተጫውቷል። የፖለቲካ ዝንባሌ እንዳለውና ምርጫ መወዳደር እንደሚፈልግም ይነገራል።

የትዳር አጋሩ ኪምበርሊ ጉይልፎይ ሐምሌ ላይ በቫይረሱ ተይዛ አገግማለች።

በትራምፕ ዙሪያ ካሉ ሰዎች ሌላው ቫይረሱ የተገኘበት አንድሪው ጁሊያኒ የተባለው አማካሪያቸው ነው።

አንድሪው የትራምፕ የግል ጠበቃ ሩዲ ጁሊያኒ ልጅ ነው።

ሲቢኤስ እንደሚለው ቢያንስ አራት የዋይት ሐውስ ሠራተኞች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል።

ትራምፕ ቫይረሱ ሲይዛቸው ሦስት ቀን ሆስፒታል ቆይተው መውጣታቸው አይዘነጋም።

ልጃቸው ትራምፕ ጁንየር አንድ ቃለ ምልልስ ላይ መገናኛ ብዙኃን የሞቱ ሰዎችን ቁጥር አጋነው እንደሚገልጹና ያገገሙ ሰዎች ቁጥር እንደሚበልጥ ተናግረው አሜሪካ ቫይረሱን እየተቆጣጠረችው እንደሆነ ገልጸዋል።

እስካሁን 11.8 ሚሊዮን አሜሪካውያን በቫይረሱ ተይዘው 253,000 ሞተዋል።