ጋን የሚያህል ጭምብል የሰሩት ሥራ ፈጣሪዎች

የፎቶው ባለመብት, VZYR TECHNOLOGIES
ላለፉት ሁለት ወራት ሥራ ፈጣሪው የዚን አል-ቃይሲ በካናዳዋ ቶሮንቶ ጎዳና ጋን የሚያህል ጭምብል አጥልቆ ነው እየዞረ ያለው።
ሃዝማት እያሉ የሚጠሩት ይህ ጭምብል ጭንቅላቱን ሸፍኖ ደረቱ ጋር ይደርሳል።
ይህ መሣሪያ ከጀርባው በባትሪ የሚሠራ አየር ማጣሪያ ተገጥሞለታል። ማጣሪያው ንፁህ አየር ያስገባና የቆሸሸውን ያስወጣል።
የ32 ዓመቱ የዚን ይህን እንደ ሆሊውድ ልብ ወለድ ፊልሞች ያለ ጋን የሚያክል ጭምብል አጥልቆ ሲጎማለል ያዩት ሰዎች መገረማቸው አልቀረም።
"አንድ ሰው ሲያየኝ 'ከየት ነው ይህን ያገኘኸው' ሲል ጮክ ብሎ ጠየቀኝ፤ ሌሎች ግን በአግራሞት ነው የሚመለከቱኝ" ይላል የዚን።
"ብዙዎቹ አይስቁም። ቢስቁስ እንዴት አድርጌ አያቸዋለሁ ጭምብል አጥልቀው?"
የዚን ብቻ ሳይሆን በርካታ የዓለማችን ሥራ ፈጣሪዎች የኮሮናቫይረስ ያመጣውን 'ዕድል' ተጠቅመው ከሌላው ለየት ያለ ጭምብል እየሠሩ ነው።
እነዚህ ጋን የሚያክሉ ጨምብሎች ከተለመደው የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ከፍ ባለ መልኩ ቫይረሱን መከላከል ያስችላሉ።
ካናዳዊው የዚን የሠራቸው ጭምብሎች ባትሪያቸው እስከ 12 ሰዓታት ድረስ ይዘልቃል። ሽያጩም ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍ እያለ እንደመጣ ሥራ ፈጣሪው ይናገራል።

የፎቶው ባለመብት, VZYR TECHNOLOGIES
የቀድሞው የአሜሪካ ባሕር ኃይል አባል የነበረው ክሪስ ኤሊንገር ሌላኛቸው ሃዝማት የሠራ ሰው ነው።
ቴክሳስ ውስጥ የሚገኘው ኩባንያው ልክ እን ደሞተር ሳይክል ሄልሜት ያሉ ጭምብሎችን እየሠራ ለገበያ ያቀርባል።
ጭምብሎቹ ከውስጥና ከውጭ ማይክሮፎን ተገጥሞላቸዋል። ይህም ሰዎች ሲናገሩ እንዲሰማና ጭምብሉን ያጠለቀ ሰው ድምፁ እንዳይታፈን በሚል ነው።
ሌላው ቀርቶ በብሉቱዝ የሚሠሩ፣ ለሙዚቃና ለስልክ ጥሪ የሚሆኑ ድምፅ ማጉያዎች ተገጥመውለታል።
ነገር ግን የኮሮናቫይረስ ክትባቶች ብቅ ብቅ ማለታቸው ለሃዝማቶች መልካም ዜና አይመስልም።
ቢሆንም ሥራ ፈጣሪዎቹ ሃዝማቶቹ ወደፊት ሰዎች ንፁህ አየር በሚያሻቸው ጊዜ ጥቅም ላይ የሚውሉ ስለሆነ ችግር የለውም ባይ ናቸው።
እኒዚህ ሃዝማቶች በጣም ትልቅ መሆናቸው ለአጠቃቀም ምቹ አይደሉም የሚል ትችት እንዲቀርብባቸው አድርጓል።
ነገር ግን በነዚህ ጭምብሎች ውስጥ የሰዎች ፊት መታየት መቻሉ ደግሞ እንደ አንድ በጎ ጎን ይወሰዳል።
ሃዝማቶች ከ149 ጀምሮ እስከ 379 ዶላር በሚደርስ ዋጋ እየተሸጡ ነው።













