ኮሮናቫይረስ፡ ኮሮናቫይረስ ውሸት ነው ብሎ የሚያምነው ጎልማሳ ባለቤቱ በበሽታው ተቀጠፈች

የፎቶው ባለመብት, FACEBOOK
ብራየን ሊ ይባላል፡፡ በፍሎሪዳ ውስጥ ታክሲ ነጂ ነው፡፡ ለረዥም ጊዜ ኮሮና የሚባል ነገር የለም፤ ፍጹም ቅጥፈት ነው ሲል ነበር፡፡ ይህን የሚለው ግን ለጨዋታ ድምቀት ሳይሆን የምሩን ነበር፡፡ እንዲያውም ወደ ፌስቡክ እየወጣ ሰዎች በዚህ እልም ያለ ውሸት እንዳይታለሉ ይሰብክ ነበር፡፡
ባለቤቱ ኤሪን ትባላለች፡፡ ወይም ‹ትባል ነበር› ማለቱ ይሻላል፡፡ በቫይረሱ ምክንያት ሕይወተወን አጥታለች።
ለብራይን ይህ ትልቁ ቅጣት ሆኖበታል፣ ዛሬ፡፡
ብራይንም ሆነ ባለቤቱ ኤሪን በበይነ መረብ የሚሰራጩ መላምቶች ሰለባ ሆነው ቆይተዋል፡፡
‹ኮሮና ብሎ ነገር የለም፡፡ ካለም ጉንፋን ነው፤ ካለም 5ጂ ቴክኖሎጂ የፈጠረው ነገር ነው› ሲሉ ነበር የሚያምኑት፡፡
ለዚህም ይመስላል ቫይረሱ ከተገኘባቸው በኋላ እንኳን ሐኪም የሚላቸውን ነገር ለመስማት ያልፈቀዱት፡፡
ሁለቱም ግንቦት ላይ ነበር የታመሙት፡፡ ብራይን በለስ ቀንቶት አገገመ፡፡ ሚስቱ ግን አሸለበች፤ 46 ዓመቷ ነበር፡፡
ብራይን በሐምሌ ወር ላይ የቢቢሲ እንግዳ ነበር፡፡ ቢቢሲ ያኔ በኮቪድ-19 ዙርያ በሚሰሩ መላምቶችና የሴራ ወሬዎች ዙርያ አንድ ዘገባ እየሰራ ነበር፡፡
ያን ጊዜ የብራይን ሚስት አልሞተችም ነበር፡፡ ሆኖም በጽኑ ሕሙማን ማገገምያ ክፍል ገብታ ትተነፍስ የነበረው በቬንትሌተር ነበር፡፡
ኤሪን በፍሎሪዳ ፓስተር ነበረች፡፡ ጤናዋ ግን መልካም የሚባል አልነበረም፡፡ አንደኛ አስም ነበረባት፤ ሁለተኛ የእንቅልፍ እጦት ያሰቃያት ነበር፡፡
ባሏ ባደረሰባት የአስተሳሰብ ተጽእኖ ምክንያት እና በወቅቱ በቫይረሱ ዙርያ በነበራቸው እምነት ምክንያት ጥንቃቄ እንዳላደረጉ ነው የሚናገረው ብራያን፣ ለቢቢሲ፡፡
ስለዚህ ቫይረሱ እንደያዛቸው ቢያውቁም ሁለቱም ሥራቸውን ቀጥለው ነበር፡፡ እሷም ፓስተርነቷን፣ እሱም ሹፍርናውን፡፡
እሷ አልጋ ከያዘች ወዲህም ቢሆን ብራይን መደንገጥ በነበረበት ደረጃ አልደነገጠም፡፡
መድኃኒት ግዛ ሲባል በመድኃኒቶቹ እምነት ባይኖረውም እያቅማማም ቢሆን ታክሲው እያሽረከረ ይሄዳል፡፡ በጉዞው ላይ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ አያደርግ? ማኅበራዊ ርቀቱን አይጠብቅ፡፡
ለነገሩ ሁለቱም ግንቦት ላይ የታመሙ ጊዜ ራሱ ቶሎ ሐኪም ለማየት አልሄዱም፡፡
በብዙ ጥርጣሬና ማመንታት ነበር ምርመራ ያደረጉት፡፡ አለባችሁ ሲባሉም አልደነቃቸውም፡፡ ምክንያቱም ኮሮናቫይረስ ብሎ ነገር የለም ብለው በውስጣቸው ያምኑ ስለነበረ፡፡
ብራይን አሁን ለቢቢሲ እንደተናገረው ‹ያን ጊዜ ሰው የሚለኝን ሰምቼ ቢሆን ኖሮ…› የሚል ጸጸት አድሮበታል፡፡
‹‹ቫይረሱ እውነት ነው፡፡ ሰዎችን በተለያየ ደረጃ ቢያጠቃም ኮቪድ-19 ሐቅ መሆኑን አምኛለሁ፡፡ አሁን ወደኋላ ሄጄ የምቀይረው ነገር ግን የለም፡፡ አሁንን መኖር ነው የሚኖርብኝ፤ አሁን ላይ ለወደፊት የተሻለ ምርጫ እያደረጉ ከመኖር ሌላ ምን ማድረግ እችላሁ?›› ብሏል ለቢቢሲ፡፡
‹‹ባለቤቴ ላትመለስ ሄዳለች፡፡ አንዳንድ ጊዜ ትናፍቀኛለች፡፡ ወደ ተሻለ ዓለም ተሸጋግራለች ብዬ ማመን ነው የምመርጠው፡፡ ›› ይላል ብራይን፡፡
እንዴት የቫይረሱን መኖር ሊክዱ ቻሉ?
ብራይን እንደሚለው እሱም ሆነ ሟች ባለቤቱ ቫይረሱ ሐሰት ነው ሲሉ ምን ማለታቸው እንደሆነ በግልጽ ለመናገር ይከብደዋል፡፡
መጀመርያ አካባቢ 5ጂ ያመጣው መቅሰፍት ነበር የሚመለስላቸው፡፡
ቀጥለው ደግሞ እንዲሁ መንግሥታት ሕዝቦቻቸውን ለማታለል የፈጠሩት አድርገው መውሰድ ጀመሩ፡፡ ይህን እምነት ያዳበሩት ደግሞ በፌስቡክ ላይ በሚያነቡት ነገር ነው፡፡
‹‹እውነቱን ለመናገር እኛ በዋናነት ይመስለን የነበረው መንግሥት ሕዝቡን ለማስቀየስና በሌላ ጉዳይ ወጥሮ ለመያዝ የፈጠረው ወሬ እንጂ ቫይረሱ የምር አይመስለንም ነበር፡፡
ብራይን ባለቤቱ ጽኑ ሕሙማን ማገገምያ ከገባች በኋላ ወደ ፌስ ቡክ ተመለሰና ‹‹በኛ ይብቃ፣ ትውልድ ይዳን›› ብሎ መጻፍ ጀመረ፡፡
በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አሁንም ድረስ ቫይረሱ ፈጠራ ነው፤ ወሬ ነው ብለው ከልባቸው ያምናሉ፡፡
ቢቢሲ ባለፈው ግንቦት በሰራው አንድ ጥናት በርካታ ሰዎች 5ጂ የቴሌኮሚኒኬሽን የስልክ መስመሮች ላይ ጉዳት አድርሰዋል፡፡ በሕክምና ባለሞያዎቸ ላይ እንዲሁ ጉዳት አድርሰዋል፡፡ በጤና ተቋማትም ላይ እንዲሁ፡፡


የብዙዎቹ የተሳሳተ እምነት ተኮትኩቶ ያደገው ታዲያ በማኅበራዊ ሚዲያ ነው፡፡
የፌስቡክ ቃል አቀባይ ለቢቢሲ ሲናገር እንዲህ ዓይነት አሳሳች መረጃዎች ሲመጡ ፌስቡክ እርምጃ ይወስድባቸዋል፡፡
ለምሳሌ ባለፉት ወራት 7 ሚሊዮን የሚሆኑ ከቫይረሱ ጋር የተያያዙ ሐሳዊ መረጃዎች ከገጹ እንዲወገዱ አድርገናል ብሏል፡፡
ሆኖም ተቺዎች ፌስቡክ ሐሳዊ መረጃዎችን ለማጥፋት ዳተኛ ነው ይላሉ፡፡
ቫይረሱ አሁን በመላው ዓለም 24 ሚሊዮን ሰዎችን አዳርሷል፡፡ የ800ሺህ ሰዎችን ሕይወት ነጥቋል፡፡
ይህ ሁሉ ግን ሐሰትና የተቀነባበረ ወሬ የሚመስለው ሰው ይኖራል ተብሎ አይጠበቅም፡፡
እውነታው ግን ሌላ ነው፡፡ አሁንም ሚሊዮኖች ኮቪድ-19 ብሎ ነገር የለም፤ ወይም መንግሥታት የፈጠሩት ቅንብር ነው ብለው ነው የሚያስቡት፡፡
በተለይም ከክትባት ጋር በተያያዘ ብዙ መላምቶች ማኅበራዊ ሚዲያውን አጥለቅልቀውታል፡፡
ቢልጌትስ የሕዝብ ቁጥርን ለመቀነስ የዘየደው ነው ከሚለው ጀምሮ፣ ገንዘብ በክትባት መልክ ለማፈስ የተፈጠረ በሽታ ነው ብለው ዛሬም ሚሊዮኖች ያምናሉ፡፡
ብዙዎች እንደ ብራያን የሚወዱትን እስኪያጡ ድረስ ከዚህ ቅዥብርብር እምነታቸው ንቅንቅ የሚሉ አይመስሉም፡፡
















