ናይጄሪያ የፖሊስን ጭካኔ ለመቃወም በወጡ ሰልፈኞች ላይ ተተኩሷል መባሉን ካደች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በባለፈው ወር የፖሊስ ጭካኔን ለመቃወም የወጡ ሰልፈኞች በጥይት ተገድለዋል መባሉን ተከትሎ የናይጄሪያ ጦር በበኩሉ ይህ አልተፈፀመም ሲል ክዷል።
ወታደሮች ሲተኩሱ የነበሩት የጎማ ጥይት ነውም ተብሏል።
ብርጋዲየር ጄኔራል አህመድ ታይዎ ይህንንም ንግግራቸውን የሚያጠናክር የቪዲዮ ማስረጃዎች ለአጣሪ ኮሚቴው አቅርበዋል።
አለም አቀፉ የመብት ተሟጋች ድርጅት አምነስቲ በበኩሉ በመዲናዋ ሌጎስ ሌኪ በምትባል ሰፈር ወታደሮች በተቃዋሚዎች ላይ በከፈቱት ተኩስ 12 ሰዎች ተገድለዋል ብሏል ባወጣው ሪፖርት።
በርካታ የአይን እማኞችም እንዲሁ ወታደሮች በተቃዋሚዎቹ ላይ ሲተኩሱ እንዳዩ ለቢቢሲ ገልፀዋል።
አንድ ሺህ የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች በባለፈው ወር መኪኖች እንዳይተላለፉ ዋነኛ ጎዳናን የዘጉ ሲሆን ተኩስ ከመጀመሩ በፊትም ወታደሮች ተቃዋሚዎቹ ያሉበትን አካባቢ ሲያጥሩ ይታያል።
ተቃዋሚዎቹ ቁጭ ብለው እጅ ለእጅ ተጠላልፈውና ብሄራዊ መዝሙር እየዘመሩ በነበረበት ወቅት ተኩሶች ይሰሙም እንደነበር በወቅቱ በማህበራዊ ሚዲያ የተጋራ ቪዲዮ ያሳያል።
ከአካባቢው የወጣ ቪዲዮ እንደሚያሳየው ተቃዋሚዎች የቆሰሉ ሰዎችን ሲንከባከቡ ያሳያል።
ጥቃቶቹ የደረሱት ዘረፋን ለማስቆም የተቋቋመውን ልዩ የፌደራል ፖሊስ ኃይል ወይም ሳርስ ተብሎ የሚታወቀው ቡድን ላይ ያነጣጠረው ተቃውሞ በከፍተኛ ሁኔታ በመቀጣጠሉ ነው።
ልዩ ኃይሉ ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ሰዎችን ማሰር፣ ማሰቃየትና ግድያም ይፈፅማል በሚልም ከፍተኛ ውግዘትም ቀርቦበታል።
በሳርስ ተፈፅመዋል የተባሉ ጥቃቶችንና ወንጀሎችን ለማጣራት ለተቋቋመው ኮሚቴም በወታደሮቻቸው ላይ ስህተት የተሞሉ መረጃዎች እንደሚሰራጩ ጄኔራል ታይዎ ተናግረዋል።
"ወንጀላቸው ከተባለ ሁላችንንም ለመጠበቅ በስራ ቦታቸው ላይ መገኘታቸው ነው" በማለትም ተናግረዋል።
ጄኔራሉ ቪዲዮውንም እያሳዩ "ጥይት ወደ ሰማይ ሲተኩሱ እዩዋቸው፤ እንዲሁም የጎማ ጥይት ነው የሚተኩሱት" ብለዋል።
አንዲት የአይን እማኝም እንዲሁ የሞተ አስከሬን መሬት ላይ እንዳየች መናገሯን ተከትሎ ጄኔራሉ "ባየችው ነገር ደንግጣ ነው" በማለት ለአጃንስ ፍራንስ ፐሬስ ተናግረዋል።
ሰዎች ሲገደሉ አይተናል ላሉም ምላሽ ይስጡ አይስጡ አልታወቀም።
ከዚህም በተጨማሪ በተቃውሞ ሰልፉ ላይ የተሳተፉትም እንዲሁም በመንግሥት ኢላማ ሆነናል ማለታቸውንም የቢቢሲ ማየኒ ጆንስ ሪፖርት ያስረዳል።
በርካታ ተቃዋሚ ሰልፈኞችና ኩባንያዎች የባንክ አካውንታቸው እንደተዘጋና የታሰሩትም ብዙ ናቸው ይላሉ። ለተቃዋሚዎቹ ጥበቃ የቆመ የህግ ባለሙያም ከአገር ልትወጣ ስትል ፓስፖርቷ ቢወሰድም ተመልሶላታል።
ከፍተኛ ተቃውሞ የቀረበበት ሳርስ እንዲበተን ቢደረግም የሳርስ አባላት በሌሎች የፖሊስ ክፍሎች እየተሰማሩና እየተመደቡ ነው የሚሉ ጉዳዮች መሰማታቸውን ተከትሎም እንደገና ተቃውሞቹ የቀጠሉት።
ሰልፈኞቹ እነዚህ የሳርስ አባላት ለፈፀሙት ወንጀል ህግ ፊት መቅረብ አለባቸውም እያሉ ነው።
የአገሪቱ ፕሬዚዳንት "ስር ነቀል" የፖሊስ ማሻሻያ እንደሚደረግና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈፅመዋል የተባሉትም የሳርስ አባላት ወደ ፍርድ ይቀርባሉ ብለው ነበር።
ተቃውሞው በዚህ ቀጥሎም በአገሪቷ ፀጥታ ኃይሎችና አገሪቷ የምትተደዳደርበት አጠቃላይ መዋቅራዊ ለውጥ ሊመጣም ይገባል የሚሉ ነበሩ።
በናይጄሪያ ያለው አምነስቲ ከሆስፒታልና የአይን እማኞች ሰበሰብኩት ባለው መረጃ "የናይጄሪያ ጦር በሺዎች በሚቆጠሩ የፖሊስን ጭካኔ ለማስቆምና መልካም አስተዳደር እንዲመጣ የሚጠይቁ ሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ ተኩስ ከፍተዋል" ብሏል።
የሌጎስ አስተዳደር 30 ሰዎች ተጎድተዋል ብሏል።
መዲናዋ ሌጎስን ጨምሮ በርካታ የናይጄሪያ ከተሞች ህንፃዎች ፈራርሰዋል፣ የመገበያያ ማዕከላት ተዘርፈዋል፣ እንዲሁም ማረሚያ ቤቶች ጥቃት ደርሶባቸዋል ተብሏል።
የናይጄሪያ ምክትል ፕሬዚዳንት በተቃውሞ ሰልፎች ላይ ጥቃት ለደረሰባቸው ሰዎች ፍትሕ እንደሚመጣ ቃል ገብተዋል።












