ፖሊስ፡ የናይጄርያ ልዩ የፖሊስ ኃይል እንዲወገድ የገፋፋው ተቃውሞ

ናይጄርያውያን ሳርስ በሚል የሚታወቀውና ዝርፊያ ላይ አተኩሮ እንዲሠራ የተቋቋመው ልዩ የፖሊስ ኃይል እንዲወገድ ጠይቀዋል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ናይጄርያውያን ሳርስ በሚል የሚታወቀውና ዝርፊያ ላይ አተኩሮ እንዲሠራ የተቋቋመው ልዩ የፖሊስ ኃይል እንዲወገድ ጠይቀዋል
ታትሟል

ናይጄርያውያን ለቀናት ተቃውሟቸውን አሰምተዋል። ሳርስ በሚል የሚታወቀውና ዝርፊያን ለማስወገድ የተቋቋመው ልዩ የፖሊስ ኃይል እንዲወገድ ጠይቀዋል።

ተቃውሞውን ተከትሎ ይህ ኃይል እንደተወገደ ቢገለጽም፤ ናይጄርያውያን ግን ውሳኔውን አላመኑበትም።

የልዩ ፖሊስ ኃይሉ አባላት ወደ ሌሎች ክፍሎች መዘዋወር ሳይሆን ለጥፋታቸው ተጠያቂ መደረግ አለባቸው ይላሉ።

ተቃውሞው ከናይጄርያ አልፎ አውሮፓና ካናዳ ደርሷል። ቡድኑ ሕግ ወጥ እስር እንደሚያካሂድ፣ ሰዎችን እንደሚያሰቃይና እንደሚገድልም ተቃዋሚዎቹ ይከሳሉ።

የንግድ ማዕከሏ ሌጎስን ዋና ዋና ጎዳናዎች በመዝጋት ተቃዋሚዎቹ ድምጻቸውን ሲያሰሙ አራት ቀናት ተቆጥረዋል።

አንዳንድ ተቃዋሚዎች ደግሞ በከተማዋ ዋነኛ አውሮፕላን ማረፊያ አቅራቢያ ሰልፍ ወጥተዋል።

ያሳለፍነው እሑድ የፖሊስ ኃይሉ እንደሚወገድ ይፋ ቢደረግም ፖሊሶች አቡጃ እና ኦዮ ውስጥ ተቃዋሚዎች ላይ አስለቃሽ ጭስ እና ጥይት መተኮሳቸው ተነግሯል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ያሳለፍነው እሑድ የፖሊስ ኃይሉ እንደሚወገድ ይፋ ቢደረግም ፖሊሶች አቡጃ እና ኦዮ ውስጥ ተቃዋሚዎች ላይ አስለቃሽ ጭስ እና ጥይት መተኮሳቸው ተነግሯል

የናይጄርያ ፖሊስ ኃላፊ ሞሐመድ አደሙ፤ በቡድኑ ተፈጽሟል የተባለውን ብዝበዛ በተመለከተ ምርመራ ይደረጋል ብለዋል።

ነገር ግን የቡድኑ አባላት ወደ ሌሎች የፖሊስ ክፍሎች ከተዘዋወሩ በኋላም በሕገ ወጥ ድርጊታቸው ይገፉበታል የሚል ስጋት በተቃዋሚዎች ተስተጋብቷል። አባላቱ ከዚህ ቀደም ለፈጸሙት ብዝበዛ ተጠያቂ ስለመደጋቸውም ግልጽ መረጃ የለም።

ተቃዋሚዎች እንደሚሉት፤ ከዚህ ቀደም የፖሊስ ኃይሉ አራት ጊዜ ይወገዳል ወይም ይሻሻላል ቢባልም አንዳችም ለውጥ አልታየም።

ያሳለፍነው እሑድ የፖሊስ ኃይሉ እንደሚወገድ ይፋ ቢደረግም ፖሊሶች አቡጃ እና ኦዮ ውስጥ ተቃዋሚዎች ላይ አስለቃሽ ጭስ እና ጥይት መተኮሳቸው ተነግሯል።

ይህም ሕዝቡ ሳርስ አልተወገደም እንዲል ምክንያት ሆኗል።

ድምጻዊው ዴቪዶ ተቃውሞውን ከተቀላቀለ በኋላ ፖሊሶች ተቃዋሚዎችን ማሰር አቁመዋል።

በናይጄርያ መዲና የሚሠራው የቢቢሲ ዘጋቢ ኢሳቅ ካሊድ እንደሚለው፤ በሺዎች የሚቆጠሩ የሳርስ ቡድን ፖሊሶች ከሥራ ከተባረሩ የጸጥታ ስጋት ሊከተል ይችላል።

የመብት ተሟጋቾች እንደሚሉት፤ ተቃዋሚዎችን ሲደበድቡ፣ ሲያስፈራሩና ያልተገባ ኃይል ሲጠቀሙ የነበሩት የሳርስ አባላት አይደሉም። ስለዚህም ነው በመላው ናይጄርያ ያለው የፖሊስ ሠራዊት ተሻሽሎ መዋቀር አለበት የሚሉት።

የተቃዋሚዎቹ ጥያቄ ምንድን ነው?

#EndSARS ወይም ሳርስ ይገታ የተሰኘው ንቅናቄ ቀጣዮቹን አምስት ቁልፍ ጥያቄዎች ያነሳል።

• የታሰሩ ተቃዋሚዎች በአፋጣኝ እንዲፈቱ

• በፖሊስ የተገደሉ ፍትሕ እንዲያገኙና ለቤተሰቦቻቸው ካሳ እንዲከፈል

• ገለልተኛ አካል ብዝበዛውን መርምሮ ጥፋተኞች ላይ እርምጃ እንዲወሰድ

• ከሳርስ ወጥተው ወደ ሌላ ኃይል የሚዘዋወሩ ፖሊሶች በገለልተኛ አካል የሥነ ልቦና ምዘና ተደርጎላቸው አዲስ ስልጠና እንዲሰጣቸው

• ፖሊሶች የዜጎችን ሕይወትና ንብረት በመጠበቃቸው ደሞዛቸው እንዲጨመር

ሳርስ እንዴት ነው የሚሠራው?

ሰሞነኛው ተቃውሞ የተቀሰቀሰው ፖሊሶች ሌጎስ ውስጥ ሁለት ወንዶችን ከሆቴል አስወጥተው አንደኛውን ሲተኩሱበት የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል ከተሰራጨ በኋላ ነው።

ክስተቱን ተከትሎ በርካቶች በፖሊስ እጅ እንግልት እንደደረሰባቸው ተናግረዋል።

የንግድ ማዕከሏ ሌጎስን ዋና ዋና ጎዳናዎች በመዝጋት ተቃዋሚዎቹ ድምጻቸውን ሲያሰሙ አራት ቀናት ተቆጥረዋል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የንግድ ማዕከሏ ሌጎስን ዋና ዋና ጎዳናዎች በመዝጋት ተቃዋሚዎቹ ድምጻቸውን ሲያሰሙ አራት ቀናት ተቆጥረዋል

የቢቢሲው ዘጋቢ ናዱካ ኦርጂኖሞ እንደሚለው፤ የሳርስ አባላት በአብዛኛው ወጣቶችን ኢላማ በማድረግ ይከሰሳሉ።

በተለይም 'ቅንጡ' የሚባሉ ወጣቶች በሳርስ አባላት እይታ ከገቡ በኋላ ጉቦ ካልሰጡ አይለቀቁም። አንዳንዶች በሐሰተኛ ክስ ይታሰራሉ ወይም ይፈረድባቸዋል። የተገደሉም አሉ።

የዓመቱ መባቻ ላይ ዓለም አቀፉ የመብት ተሟጋች አምንስቲ ቢያንስ 82 ሰዎች እንደተሰቃዩ እንዲሁም የተገደሉም እንዳሉም መረጃ አለኝ ብሎ ነበር።

አብዛኞቹ ከ18 እስከ 35 ባለው እድሜ ክልል ያሉ ከድሃ ቤተሰብ የተገኙ ወንዶች ናቸው። በዱላ እና በገጀራ የተደበደቡት ግለሰቦች ሕክምና መከልከላቸውን የገለጸው አምንስቲ፤ "የሚደርሰው ስቃይ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሕጎችን ይጻረራል" ሲልም አክሏል።

ማሻሻያው ለምን ውጤት አላመጣም?

#EndSARS የተባለው ሀሽታግ (ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ አንዳች ንቅናቄን በመጠሪያው ለማግኘት የሚውል) ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቅም ላይ የዋለው ከሁለት ዓመት በፊት ነበር።

ከሳምንት በፊት ንቅናቄው ዳግም አንሰራርቷል።

ከዚህ ቀደም ልዩ የፖሊስ ኃይሉን ለማሻሻል ተሞክሮ ነበር። እንደ ጎርጎሮሳውያኑ 2018 ላይ ምክትል ፕሬዘዳንት የሚ ኦሲንባጆ ቡድኑ እንዲፈርስ ውሳኔ አሳልፈው ነበር።

አምና ግን ቡድኑ ውስጥ ማሻሻያ የሚያደርግ አካል ተቋቋሞ፤ ዜጎችን በዝብዘዋል የተባሉ ፖሊሶች እንዲባረሩና ለፍርድ እንዲቀርቡም ምክረ ሐሳብ ሰጠ።

በወቅቱ ፕሬዘዳንት ሙሐመዱ ቡሐሪ የፖሊስ ሠራዊት ኃላፊ ምክረ ሐሳቡን በሦስት ወራት እንዲተገብሩ መመሪያ አስተላልፈዋል።

ተቺዎች እንደሚሉት ግን ለውጡ ውስን ነበር።

ሳርስ ላይ ማሻሻያ እንዲደረግ 2017 ላይም ተወስኖ ነበር። ያኔ አንድ ግለሰብ በፖሊስ ሲገደል የሚያሳያይ ተንቀሳቃሽ ምስል መሰራጨቱን ተከትሎ ነበር ውሳኔው የተላለፈው።

2010 ላይም ቡድኑ ሳተላይት ኃላፊዎችን ያባር ተብሏል።

በተለያየ ጊዜ እነዚህ ሁሉ ውሳኔዎች ቢተላለፉም ግን ቡድኑ ሥራውን መቀጠሉን የቢቢሲ ዘጋቢ ማዬኒ ጆንስ ትናገራለች።