የአሜሪካ ምርጫ፡በስተመጨረሻም ቻይና ጆ ባይደንን እንኳን ደስ አለዎት አለች

ጆ ባይደንና ሺ ዢንፒንግ

የፎቶው ባለመብት, Reuters/EPA

ታትሟል

ቻይና ከረጅም ቀናት ቆይታ በኋላ በስተመጨረሻም ለቀጣዩ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክቷን አስተላልፋለች።

ጆ ባይደን የአሜሪካ ቀጣዩ ፕሬዝዳንት ሆነው መመረጣቸውን ተከትሎ በርካታ የዓለማችን መሪዎች እንኳን ደስ አለዎት ለማለት ፈጥነው ነበር።

ነገር ግን ሁሉም የዓለም አገር መሪዎች በአንድ ድምጽ የጆባይደን ፕሬዝዳንት ሆኖ መመረጥ ደስታ እንደፈጠረባቸውና አብረው ለመስራትም ዝግጁ መሆናቸውን አልገለፁም።

በተመራጭ ፕሬዝዳንቱ መመረጥ የተሰማቸውን ካልገለፁ የዓለማችን መሪዎች መካከል የሩሲያው ፕሬዝዳንት እና የቻይናው ፕሬዝዳንት ዋነኞቹ ናቸው።

''የአሜሪካ ሕዝብ ምርጫን እናከብራለን። ለጆ ባይደን እና ካማላ ሀሪስ እንኳን ደስ አላችሁ ለማለት እንወዳለን'' ብለዋል የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መስሪያ ቤት ቃል አቀባይ።

የቻይና እና አሜሪካ ግንኙነት ለሁለቱም ወገኖች እጅግ ጠቃሚ ነው፤ ለተቀረውም ዓለም። በቅርብ ዓመታት ከንግድ ጋር በተያየዘ ሁለቱ አገራት ፍጥጫ ውስጥ ገብተው የነበረ ሲሆን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ደግሞ ነገሮችን አባብሶታል።

የሩሲያው ፕሬዝዳንት ለጆ ባይደን እስካሁን እንኳን ደስ አለዎት አላሉም።

ከአራት ዓመት በፊት ፕሬዝዳንት ፑቲን ዶናልድ ትራምፕ ማሸነፋቸውን ተከትሎ ቀድመው እንኳን ደስ አለዎት ካሉ መሪዎች መካከል አንዱ ነበሩ።

አሁን ግን ምንም ዓይነት የትዊት፣ የቴሌግራም ወይንም የስልክ መልዕክት አልላኩም። የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲምትሪ ፔስኮቭ እንኳን ደስ አለዎት ለማለት የዘገዩት ፕሬዝዳንት ትራምፕ የምርጫውን ውጤት በማስመልከት የመሰረቱት ክስ ነው ብለዋል።

''እኛ ትክክለኛው ነገር ብለን የምናስበው የምርጫው ውጤት በይፋ ሲገለጽ ነው'' ብለዋል ከሮይተርስ ጋር በነበራቸው ቆይታ። ነገር ግን ሞስኮ የሚገኘው የቢቢሲው ዘጋቢ ስቲቭ ሮዝንበርግ ከሞስኮ በኩል የእንኳን ደስ አለዎት መልእክት አለመላኩ በውጤቱ ደስተኞች አለመሆናቸውን ያስጠረጥራል ይላል።

ሌላኛው ምንም አስተያየት ያልሰጡት የቱርኩ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ታይብ ኤርዶጋን ናቸው።

በ2016 በተካሄደው የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ዶናልድ ትራምፕ ማሸነፋቸው ከተነገረ ከአንድ ቀን በኋላ የቱርኩ ፕሬዝዳንት ስልክ በመደወል የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክታቸውን አስተላልፈው ነበር።

በተመሳሳይ 2012 ላይ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ሲያሸንፉ እንኳን ደስ አለዎት ብለው ነበር።

ኤርዶጋን ከፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ጠበቅ ያለ ግንኙነት ያላቸው ሲሆን ባለፉት አራት ዓመታት አሜሪካ ቱርክ ላይ በሩሲያ በኩል ሊጣሉ የሚችሉ ማዕቀቦችን መከላከል ችላለች።

የሰሜን ኮሪያው ፕሬዝዳንት ኪም ጆንግ ኡንም ቢሆኑ እስካሁን ጆ ባይደንን እንኳን ደስ አለዎት አላሏቸውም። በ2016 ተካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ዶናልድ ትራምፕ ማሸነፋቸው ከተገለጸ ከቀናት በኋላ ፒዮንግያንድ ትራምፕን እንኳን ደስ አለዎት ብለው ነበር።