ኮሮናቫይረስ ፡ ግብጻዊው የሊቨርፑል አጥቂ ሞሐመድ ሳላህ በኮሮናቫይረስ ተያዘ

ሞ ሳላህ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

የሊቨርፑል አጥቂ የሆነው ግብጻዊው ሞሐመድ ሳላህ ከአገሩ ቡድን ጋር በዓለም አቀፍ ውድድር ላይ እያለ በተደረገለት ምርመራ የኮሮናቫይረስ እንደተገኘበት ተገለጸ።

የግብጽ እግር ኳስ ማኅበር ትናንት እንዳስታወቀው የ28 ዓመቱ ሳላህ የተደረገለት ምርምራ ወረርሽኙ እንዳለበት ቢያረጋግጥም፤ ነገር ግን እግር ኳስ ተጫዋቹ ላይ ምንም አይነት የበሽታው ምልክቶች አልታዩበትም።

ማኅበሩ ጨምሮ ይፋ እንዳደረገው የእግር ኳስ ኮከቡ ሞሐመድ ሳላህ ላይ ሁለተኛ ዙር ምርመራ መደረጉንና ኮሮናቫይረስ እንዳለበት መረጋገጡን ገልጿል።

"ሳላህ በአሁኑ ጊዜ መንፈሱ ጠንካራ እንደሆነ ያለ ሲሆን፤ ምንም አይነት የበሽታው ምልክት አይታይበትም" ሲል የግብጽ እግር ኳስ ማኅበር ባወጣው መግለጫ ላይ ጠቅሷል።

ማኅበሩ ጨምሮም ከሳላህ ውጪ ያሉት ሌሎች የቡድኑ አባላት ላይ በተደረገው ምርመራ ከበሽታው ነጻ መሆናቸው ታውቋል።

ግብጽ በአገሯ ላይ ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከቶጎ ብሔራዊ ቡድን ጋር ዛሬ ቅዳሜ ግጥሚያ የምታደርግ ሲሆን፤ የመልስ ጨዋታው በመጪው ማክሰኞ ቶጎ ውስጥ ይካሄዳል።

ሳላህ ቫይረሱ ከተገኘበት በኋላ በአሁኑ ወቅት ራሱን ለይቶ የሚገኝ ሲሆን በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግና በአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ውድድሮች ላይ ቡድኑ ሊቨርፑል በሚያደርጋቸው ቀጣይ ሁለት ጨዋታዎች ላይ ላይሰለፍ ይችላል ተብሏል።

በዚህም ሊቨርፑል በመጪው ሳምንት እሁድ በፕሪሚየር ሊጉ ከሌስተር ጋር እንዲሁም እሱን ተከትሎ ረቡዕ በሻምፒየንስ ሊግ ከጣሊያኑ የአታላንታ ቡድን ጋር በሚኖረው ጨዋታ ላይ ላይገኝ ይችላል።

ሞሐመድ ሳላህ እየተካሄደ ባለው የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ላይ ቡድኑ በተጋጠመባቸው ስምንት ጨዋታዎች ላይ ተሰልፎ ስምንት ግቦችን ለማስቆጠር ችሏል።

ሊቨርፑል ከዓመታት ከረጅም ዓመታት በኋላ በሞሐመድ ሳላህ ወሳኝ አስተዋጽኦ የባለፈውን ወቅት የፒሪሚየር ሊግ ዋንጫን ማንሳቱ አይዘነጋም።

ኮሮና