ሳኡዲ አረቢያ፡ አከራካሪው የካፋላ ሥርዓት በመጠኑ ማሻሻያ ተደረገበት

የፎቶው ባለመብት, AFP
ሳኡዲ አረቢያ እስከ 10 ሚሊየን የሚደርሱ ስደተኛ ሰራተኞችን በቀጥታ ይመለከታል የተባለለትና ቀጣሪዎች ሰራተኞቻቸውን ሙሉ በሙሉ እንዲቆጣጠሩ የሚያስችለውን ሕግ በመጠኑም ቢሆን ለመቀነስ ማሰቧን አስታውቃለች።
በተሻሻለው ሕግ መሰረት በግል ድርጅቶች ተቀጥረው የሚሰሩ ሰራተኞች የአሰሪዎቻቸውን ይሁንታ ሳይጠብቁ ሥራ መቀየርና ከአገር መውጣት ያስችላቸዋል ተብሏል።
የሳኡዲ መንግስት በአገሪቱ ያለውን የሥራ ሂደት ለማቀላጠፍና ውጤታማነትን ለመጨመር እየሰራ እንደሆነ መግለጹ የሚታወስ ነው።
በርካታ በሳኡዲ አረቢያና በአረብ አገራት የሚሰሩ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች እንደሚሉት 'ካፋላ' የሚባለው ሥርዓት ተቀጣሪዎችን ለተለያዩ ጥቃቶች የሚያጋልጥና መብታቸውን የሚጋፋ ነው።
በካፋላ ሥርዓት መሰረት ሰራተኞቹ ቢጎዱና ቢንገላቱም እንኳን ካለ አሰሪዎቻቸው ፈቃድ ከአገር ሊወጡም ሆነ ወደ ሌላ የስራ አይነት መዘዋወር አይችሉም።
በአገሪቱ የሰው ኃብት ሚኒስቴር መስሪያ ቤት መረጃ መሰረት፤ የተሻሻለው ሕግ ረቡዕ ዕለት ይፋ የተደረገ ሲሆን ሁሉም በግል የስራ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ የውጭ አገር ዜጎችንተጠቃሚ የሚያደርግ ነው።
ከመጪው መጋቢት ጀምሮ ደግሞ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ መደረግ ይጀምራል ብሏል ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ባወጣው መግለጫ።
በሂዩማን ራይትስ ዋች ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ሮትና ቢገም እንደሚሉት፤ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ያስተዋወቀው አዲሱ ማሻሻያ ''በጣም ወሳኝና የበርካታ ስደተኞችን ሕይወት የሚቀይር ነው።''
አክለውም ''ነገር ግን ይህ ማሻሻያ እንጂ ሙሉ በሙሉ የካፋላ ስርአትን የሚያጠፋ አይደለም'' ብለዋል።
ምንም እንኳን በሥርዓቱ ላይ ማሻሻያ ቢደረግም ከሌላ አገር የሚመጡ ሰራተኞች አሁንም ወደ ሳኡዲ አረቢያ ለመግባት የቀጣሪ ድርጅት ይሁንታ የሚፈልጉ ሲሆን፤ ከክፍያ ጋር የተያያዘው ጉዳይም አሁንም ምላሽ አላገኘም።
''ይህ ማለት አሁንም ሰራተኞቹ ብዝበዛ ሊደርስባቸው ይችላል። አሁንም ቢሆን ከፍተኛው ስልጣንና ተሰሚነት ያላቸው ቀጣሪ ድርጅቶቹ ናቸው'' ብለዋል።
''በተጨማሪም ይህ አዲስ ማሻሻያ በግል ድርጅቶች ተቀጥረው ለሚሰሩ እንጂ በቤት ሰራተኝነት ለሚሰሩት አይደለም። በአሁኑ ሰአት ግን በከፍተኛ ሁኔታ ጉዳት እየደረሰባቸውና እየተሰቃዩ የሚገኙት የቤት ሰራተኞች ናቸው።''
በሳኡዲ አረቢያ ከፍተኛ እንግልት እንደሚደርስባቸው የሚነገረው የቤት ሰራተኞች ማግኘት የሚገባቸው ክፍያ፣ ዓመታዊ ፈቃድ፣ የሳምንት እረፍት እንዲሁም በቀን ውስጥ ምን ያህል ሰዓት መስራት አለባቸው የሚለው በሙሉ እንዳይመለከታቸው ተደርጓል።












