ኮሮናቫይረስ፡ የካፍ ፕሬዝደንት በኮሮናቫይረስ ምክንያት ሆስፒታል ገቡ

የፎቶው ባለመብት, Confederation of African Football
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን - ካፍ ፕሬዝደንቱ አህመድ አህመድ በኮሮረናቫይረስ ከተያዙ በኋላ ለአምስት ቀናት ሆስፒታል ውስጥ ሊቆዩ እንደሆነ ተገልጿል።
የ60 ዓመቱ ፕሬዝዳንት ኮሮናቫይረስ የተገኘባቸው አርብ ዕለት ሲሆን ከሁለት ቀናት በፊት ከሞሮኮ ወደ ግብጿ መዲና ካይሮ ተጉዘው ነበር።
ለጉዟቸው ምክንያቱ ደግሞ እሁድ የተካሄደውን የኮንፌደሬሽን ዋንጫ ፍጻሜ ጨዋታ ለመታደም ነበር።
''ፕሬዝዳንቱ በዶክተሮቻችን ምክር መሰረት ለአምስት ቀናት ሆስፒታል ሊያሳልፉ እንደሆነ አውቀናል'' ሲሉ የካፍ የግንኙነት ዳይሬክተሩ አሌክስ ሲዌ ለቢቢሲ ስፖርት አፍሪካ ገልጸዋል።
ዛሬ ረፋዱ አካባቢ የአፍሪካ እግር ኳስ አስተዳዳሪው አካል ማዳጋስካራዊው ፕሬዝዳንት ለሁለት ሳምንታት እራሳቸውን አግልለው እንደሚቆዩ ገልጾ ነበር።
''ረቡዕ ዕለት ካይሮ ከደረሱ በኋላ ፕሬዝዳንቱ ቀለል ያለ የጉንፋን ምልክት ኣሳይተው ነበር። ወዲያውም በአሰራራችን መሰረት የኮቪድ-19 ምርመራ ተደርጎላቸዋል'' ብሏል ካፍ ባወጣው መግለጫ።
''ዛሬ ፕሬዝዳንቱ በኮሮረናቫይረስ መያዛቸው ተረጋግጧል። ለሚቀጥለሉት 15 ቀናትም እራሳቸውን በሆቴል ውስጥ አግልለው እንዲቆዩ ይደረጋል። እንዲሁም ባለፉት ሰባት ቀናት ከአህመድ ጋር ንክኪ የነበራቸው በተለይም በሞሮኮው ጉዞ ወቅት የተነካኩ ሰዎች መረጃው ቶሎ እንዲደርሳቸው ተደርጓል፤ ተገቢውን እርምጃም ይወስዳሉ'' ይላል መግለጫው።
ፕሬዝዳንት አህመድ በሞሮኮው አርኤስ በርካኔ አሸናፊነት የተጠናቀቀውን የኮንፌደሬሽን ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ ለማየት ነበር ወደ ሞሮኮ ያቀኑት።
ፕሬዝዳንቱ በኮሮረናቫይረስ ከመያዛቸው በፊትም ከባድ ሳምንት ነበር ያሳለፉት። ለቀጣይ ዙር ፕሬዝዳንታዊ ፉክክር መወዳደር እንደሚፈልጉም ያሳወቁት ረቡዕ ዕለት ነበር። ነገር ግን አህመድ በድጋሚ ፕሬዝዳንት እንዳይሆኑ ሊደረግ እንደሚችል ተዘግቧል።
ቢቢሲ ስፖርት አፍሪካ ባገኘው መረጃ መሰረት ደግሞ ፕሬዝዳንቱ በርካታ የስነምግባር ደንቦችን እንደጣሱና በሚቀጥለው ወር ደግሞ ክስ እንደሚቀርባቸው ይጠበቃል።
በዚህም መሰረት ፕሬዝዳንቱ የትኞቹ እጩዎች ተፎካካሪያቸው እንደሚሆኑ ከሆቴላቸው ሆነው ይከታተላሉ ማለት ነው። ለሚቀጥሉት 15 ቀናትም በሆቴላቸው ስለሚሆኑ የእጩዎች ምዝገባ ከመጠናቀቁ አንድ ቀን በፊት እራሳቸውን ካገለሉበት ሆቴል እንደሚወጡም ይጠበቃል።












