ኮሮናቫይረስ፡ የለንደን ፖሊስ ክልከላዎችን በመተላለፍ ሰልፍ የወጡ ሰዎችን አሰረ

ተቃዋሚዎች በለንደን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

በለንደን ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ የተጣለውን የእንቅስቃሴ ገደብ ለመቃወም ከወጡ ሰዎች መካካል 18 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ፖሊስ አስታወቀ።

ውሳኔውን የተቃወሙ በርካታ ሰዎች ከዩናይትድ ኪንግደም ንጉሳውያን መኖሪያ በሆነው ባኪንግሃም ቤተ-መንግስት ፊትለፊት ተሰባስበው ነበር። በመቀጠል ተቃዋሚ ሰልፈኞች ወደ ትራፋልጋር አደባባይ አምርተዋል።

ለተቃውሞ የወጡ ሰዎች በኮቪድ ምክንያት የተነጠቅነው ነጻነት ይመለስልን ሲሉ ድምጻቸውን አሰምተዋል።

የሜትሮፖሊታን ፖሊስ ተቃዋሚ ሰልፈኞቹ እንዲበተኑ የተደረገ ቢሆንም ዜጎች ግን አሁንም ቢሆን አካላዊ ርቀታቸውን መጠበቅ እንዳለባቸው ማሳሰቢያ ተላልፏል።

በዌስትሚኒስተር ድልድይ ላይ ደግሞ ፖሊስ ተቃዋሚ ሰልፈኞችን ለመበተን ጥረት በሚያደርግበት ወቅት አንዳንድ ችግሮች ተፈጥረው ነበር ተብሏል። የፖሊስ አባላት ቀላል የሚባል ጉዳት ደርሶባቸዋል።

ፖሊስ ሰልፈኞቹ በቁጥጥር ሥር ያዋልኩት የተለያዩ ሕግጋቶችን በመተላለፍ ነው ብሏል። ከጥፋቶቹ መካከልም የኮሮረናቫይረስ ሕጎችን በመጣስ፣ የአደጋ ጊዜ ሰራተኛ ላይ ጉዳት ማድረስና ነውጠኝነት በዋነኛነት ተጠቃሽ ናቸው።

ለንደን በያዝነው ሳምንት ከወረርሽኙ ጋር በተያያዘ ጠበቅ ያሉ ገደቦች ተጥለውባታል።

''ሰዎች በተቃውሞ ሰልፉ ላይ ሲገኙ አካላዊ ርቀታቸውን አለመጠበቃቸውና የተቀመጡ ሕግና ደንቦችን አለማክበራቸው በእጅጉ አሳስቦናል'' ብለዋል የሜርሮፖሊታን ፖሊስ አዛዡ ኮማንደር አዴ አዴሌካን።

አክለውም ''የተቃውሞ ሰልፉ አዘጋጆች የሰዎችን ደህንነት ለመጠበቅ በቂ ዝግጅት አላደረጉም። በዚህ ሰአት ነው የህብረተሰቡን ደህንነት ለማረጋገጥ በማሰብ ፖሊሶች የተሰበሰቡትን ሰዎች ለመበተን የተንቀሳቀሱት'' ብለዋል።

''አብዛኛዎቹ የተሰበሰቡት ሰዎች የፖሊስ አባላቱ የነገሯቸውን በመስማታቸውና አካባቢውን ቶሎ በመልቀቃቸው ደስተኞች ነን። ነገር ግን ጥቂቶች ተባባሪ ለመሆን ፈቃደኛ አልነበሩም። ሆነ ብለው ፖሊሶች የሚነግሯቸው ነገር ችላ ሲሉ ነበር። ዌስትሚኒስተር ድልድይንም ዘግተው ነበር'' ብለዋል።