ሶሪያውያን በፈንጅ በተገደሉት ሐይማኖት መሪያቸው ሞት ሐዘን ላይ ናቸው

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በሶሪያዋ መዲና ደማስቆስ ሐሙስ ዕለት መኪና ላይ በተጠመደ ፈንጂ ሕይወታቸው ያለፈው የሱኒ ሙስሊም የሐይማኖት አባት (ሙፍቲ) የቀብር ስነስርአት ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መገኘታቸው ተዘግቧል።
ሼክ ሞሀመድ አድናን አል አፊዩኒ ከከተማዋ ወጣ ባለ አካባቢ ሲደርሱ መኪናቸው ላይ የተጠመደው ቦንብ መፈንዳቱን ተከትሎ ነው ሕይወታቸው ያለፈው።
የሐይማኖት መሪው በደማስቆስ አካባቢ ከሚገኙ አማጺያን ጋር ድርድር በማድረግ የሚታወቁና የፕሬዝዳንት ባሽር አል አሳድ ደጋፊ የሆኑ ሰው እንደነበሩ ተዘግቧል።
ከዘጠኝ ዓመታት የእር በርስ ጦርነት በኋላ መንግሥት በአሁኑ ሰአት አብዛኛውን የአገሪቱን ክፍል ተቆጣጥሯል።
ከ380 ሺ በላይ የሚሆኑ ሰዎች በዚሁ የእርስ በርስ ጦርነት የተገደሉ ሲሆን ግማሽ የሶርያ ህዝብ ወይም 13.2 ሚሊየን የሚሆኑት ዜጎች ደግሞ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በሌሎች አገራት ይገኛሉ ብሏል የተባበሩት መንግስታት።
ሼክ ሞሀመድ አድናን አል አፊዩኒ ከዋና ከተማዋ በስተሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ በምትገኘው ቁድሳያ ከተማ ውስጥ ሕይወታቸው እንዳለፈ ሳና የዜና አውታር ዘግቧል። በተጨማሪም ጉዳት የደረሰበትን የሼኩ መኪና ምስልም አጋርቷል።
ሀዘንተኞች የሼኩን አስክሬን አጅበው ወደ ታሪካዊው ኦማያድ መስጂድ የሄዱ ሲሆን የቀብር ስነስርአቱም እዛው ተፈጽሟል።
ሼክ ሞሀመድ አድናን አል አፊዩኒ አጥባቂ የእስልምና መምህር ሲሆኑ ፕሬዝዳንት በሽር አል አሳድ በአውሮፓውያኑ 2016 ከአማጺያን ጋር ለደረሱት ስምምነት ከፍተኛ ሚና መጫወታቸው ይነገራል።
በሶሪያው የእርስ በርስ ጦርነት እነማን እየተዋጉ ነው?
ለፕሬዝዳንት አሳድ ድጋፍ የሚሰጡት
- ሩሲያ - በአየር ጥቃትና በተባበሩት መንግሥታት ውስጥ የፖለቲካ እገዛ በማድረግ
- ኢራን - በጦር መሳሪያ፣ በጦር አማካሪዎች እና በተዋጊ ጦር አቅርቦት
- ሄዝቦላህ - በሺህዎች የሚቆጠሩ ተዋጊዎችን በማቅረብ
- የሺአ ሙስሊም ታጣቂዎች - በኢራን በኩል ከኢራቅ፣ ከአፍጋኒስታንና ከየመን በመመልመል
በተቃዋሚዎች በኩል
- ቱርክ - በጦር መሳሪያ አቅርቦት፤ በወታደራዊና ፖሊቲካዊ ድጋፍ
- የባህረ ሰላጤው የአረብ አገራት - በገንዘብና በጦር መሳሪያ አቅርቦት
- አሜሪካ- በጦር መሳሪያ፣ በስልጠናና ለለዘብተኛ ቡድኖች ወታደራዊ ድጋፍ
- ዮርዳኖስ - በቁሳዊ ድጋፍና በስልጠና
የአካባቢው ፖለቲካዊ ተንታኞች እንደሚሉት በጎረቤት አገር ሊባኖስ ያለው ኢኮኖሚያዊ ቀውስ በሶሪያ ላይ ለወራት ከፍተኛ ጫና አሳድሯል።
ከሊባኖስ ባንኮች ሰዎችና ድርጅቶች የሚያወጡት የገንዘብ መጠን መገደብ የአሜሪካ ዶላር ወደ ሶሪያ እንደልብ እንዳይገባ አድርጎታል።
በዚህም ምክንያት በሶሪያ ሁሉም ነገር እጅግ ውድ እየሆነ መጥቷል።












