ቅርስ፡ 2ሺህ ዓመታትን ያስቆጠረ የድመት ቅርጽ ፔሩ ውስጥ ተገኘ

የድመት ቅርጽ

የፎቶው ባለመብት, EPA

ታትሟል

2ሺህ ዓመታትን ያስቆጠረ የድመት ቀርጽ በፔሩ ተራራማ ስፍራ ላይ ተገኘ።

የድመቱ ቅርጽ ይተገኘበት ስፍራ በዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ተብሎ የተመዘገበ ቦታ ሲሆን በርካታ የመሬት ላይ ቅርሶችን የያዘ ቦታ ነው። ቅርሶቹም እስከ 2000 ዓመታት ድረስ ያስቆጠሩ ናቸው።

ተመራማሪዎች እንደገለጹት ይህ ትልቅ የድመት ቅርስ በከፍታ ቦታው ላይ የተሰራው ደማቅ ቀለም ያለውን የበረሃ አፈር በመጠቀም ነው።

የድመቱ ቅርጽም እስከዛሬ ድረስ ሳይታወቅ ቆይቷል። በቅርቡ ግን በከፍታ ቦታው ላይ የምርምር ቦታ ለማቋቋም በማሰብ መንገድ ለመስራት ሲሞከር ነው ግዙፉ የድመት ቅርጽ የተገኘው።

በከፍታ ቦታው ላይ ጋደም ያለው ድመት ቅርጽ አካባቢው ለመጎብኘት ለሚመጡ ሰዎች ምቹ ቦታ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል።

የፔሩ ባህል ሚኒስትር ባወጣው መግለጫ ላይ ''ቅርሱ ሳይገኝ በመቆየቱ መስመሮቹ ሊጠፉ ተቃርበው ነበር'' ያለ ሲሆን ''አካባቢው ተራራማ በመሆኑ በተፈጥሮአዊ መንገድ ተሸርሽሮ የመጥፋት እድሉ ከፍተኛ ነበር'' በማለት ሁኔታውን ገልጿል።

ሚኒስቴሩ አክሎም ጂኦግሊፊክስ በመባል የሚታወቀው ይህ የቅርስ አይነት 37 ኪሎ ሜትር እርዝማኔ እንዳለው የገለጸ ሲሆን አካባቢው ተጸድቶ ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ እንክብካቤ እየተደረገለት ነው።

የፔሩ ዋና አርኪዮሎጂስት የሆኑት ጆኒ ኢስላ ኢፍ ለተሰኘው የዜና ወኪል ሲናገሩ በከፍታ ቦታው ላይ የተቀረጸው የድመት ምስል የናዝካዎችን ባህል የሚያሳይና ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ200 እእከ 700 ክፍለ ዘመን ባለው ጊዜ ውስጥ የተሰሩ ሊሆኑ ይችላሉ ብለዋል።